በቦኮ ሃራም ጥቃት 17 የቻድ ወታደሮች እና 96 አማፂያን መገደላቸውን የሀገሪቱ ጦር አስታወቀ

ፋይል - የቻድ ፕሬዝዳንት ማሃማት ዴቢ ኢትኖ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቃለ መሃላ ሲፈፅሙ - ግንቦት 23፣ 2024

የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ቅዳሜ እና እሁድ በወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ባደረሱት ጥቃት 17 የቻድ ወታደሮች መግደላቸውን የቻድ ጦር አስታወቀ። በጥቃቱ ወቅት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 96 የሚሆኑ አማፂያን መገደላቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

የጦሩ ቃል አቀባይ ጀነራል ኢሳክ አቼክ እሁድ ምሽት በሀገሪቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በቻድ ሐይቅ ክልል ጥቃቱ የተፈፀመው ቅዳሜ ምሽት መሆኑን ተናግረዋል። የቻድ ሐይቅ አካባቢ በዚህ አመት ከቦኮ ሃራም እና የምዕራብ አፍሪካ እስላማዊ መንግስትን ጨምሮ በአማፂያን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሶበታል።

ባለፈው ወር በወታደራዊ ካምፕ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 40 ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ፣ ፕሬዝዳንት ማሃማት ዴቢ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎችን ከቻድ ሐይቅ ለማትፋጥ ዘመቻ አካሂደው ነበር።

የምዕራባውያንን የትምህርት አሰጣጥ በመቃወም ያለፉትን አስር አመታት ትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የቆየው ቦኮ ሃራም፣ በናይጄሪያ በእስላማዊ ሕግ የሚተዳደር መንግስት ማቋቋም ይፈልጋል። አማፂ ቡድኑ፣ ካሜሩን፣ ኒጀርን እና ቻድን ጨምሮ፣ በምዕራብ አፍሪካ ወደሚገኙ የአፍሪካ አገራትም ተስፋፍቷል።

ወደ 18 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ቻድ፣ በዴቢ ኢትኖ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው አወዛጋቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት እና በኃላ በፖለቲካዊ ውዥንብር ስትታመስ ቆይታለች።