አሪዞና ላይ ድል  የቀናቸው ትራምፕ የሁሉም "ስዊንግ " ግዛቶች አሸናፊ ሆኑ

ነሐሴ 22.2024 የተነሳው ምስል የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከብሔራዊ ድንበር ጠባቂ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፖል ፔሬዝ ጋር የዩ ኤስ ደቡባዊ ድንበርን ሲጎበኙ ያሳያል ።

በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ የአሪዞናን ግዛት ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የዜና አውታሮች መተንበያቸውን ተከትሎ ፣ ሪፐብሊካኑ ሰባቱንም ተለዋዋጭ ድጋፍ ሰጪ ግዛቶች ( ስዊንግ ግዛቶች ) ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸው እርግጥ ሆኗል።

ብዙ የሂስፓኒክ ህዝብ በሚኖርበት የደቡብ ምዕራብ አሜሪካው ግዛት ከተደረገው አራት ቀናት የፈጀ ቆጠራ በኋላ ፣ ሲ ኤን ኤን እና ኤን ቢ ሲ ትራምፕ ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስን በማሸነፍ የግዛቱን 11 የምርጫ ድምፅ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል።

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እ.ኤ.አ. በ 2020 አሪዞና ውስጥ ጠባብ ግን ወሳኝ ድል በማስመዝገባቸው ትራምፕ ከመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው በኃላ ለሽንፈት ተዳርገዋል።

የህንጻ ግንባታ ዘርፍ ባለ ሀብቱ ትራምፕ ፣ በ4 ሚሊዮን ድምጽ ብልጫ የህዝብ ድምጽ ማሸነፋቸውን ጨምሮ ፣ ትራምፕ ያሳዩት ጥንካሬ እና ማንሰራራት በተሸናፊው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ሪፐብሊካኖች ቀደም ሲል የሀገሪቱን ሴኔት የተቆጣጠሩት ሲሆን ፣ለነጭ ሰራተኞች መደብ እና ግዙፍ ሂስፓኒክ መራጮች ድርሻ ምስጋና ይግባና በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አብላጫውን ለመያዝም የተቃረቡ ይመስላሉ ።

ሲ ኤን ኤን ሪፐብሊካኖች እስካሁን 213 ወንበሮችን መቆጣጠራቸውን አስታውቋል ።በታህታይ ምክር ቤቱ አብላጫ ለማግኘት 218 ወንበሮችን ማሸነፍ ያስፈልጋል።

የዜና አውታሮቹ መረብ ዴሞክራቶች 205 ወንበሮችን መቆጣጠራቸውን ያመላክታል። የፓርቲው አንጋፋ ፖለቲከኞች ግን ምክር ቤቱን በጠባብ ልዩነት በማሸነፍ በዶናልድ ትራምፕ ኃይል ላይ ልጓም ለማበጀት ተስፋ ሰንቀዋል ።

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ያሸነፏቸው ስድስት ተቀያያሪ ድጋፍ ሰጪ "ስዊንግ" ግዛቶች ፣ ፔንሲልቫንያ ፣ ዊስካንሲን ፣ሚቺጋን ፣ ሰሜን ካሮላይና ፣ ኔቫዳ እና ጆርጂያ ናቸው(ኤ ኤፊ ፒ)።