ዩክሬን ቁጥራቸው ቢያንስ 34 በሚሆን ሰው ዐልባ አይሮፕላኖች በዛሬው ዕለት ሞስኮ ላይ ጥቃት አደረሰች ።ጦርነቱ ከጀመረበት ከአውሮፓዊያኑ 2022 ወዲህ በሩሲያ መዲና ላይ ከደረሱት የድሮን ጥቃቶች ሁሉ ግዙፉ እንደሆነ የተነገረለት ጥቃት በሶስት የከተማዋ የአየር ማረፊያዎች በረራዎች እንዲታጠፉ አድርጓል ፣ በትንሹ በአንድ ሰው ላይም ጉዳት አድርሷል።
የሩስያ አየር መከላከያዎች በሌሎች የምዕራብ ሩሲያ ክልሎች ውስጥ በሶስት ሰዓት ውስጥ ሌሎች 36 ሰው አልባ አይሮፕላኖች ማምከናቸውን የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
"በሩሲያ ፌዴሬሽን ግዛት ላይ የኪየቭ አገዛዝ መደበኛ አይሮፕላን መሳይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ሙከራ ከሽፏል" ብሏል ሚኒስቴሩ።
የሩስያ ፌደራል አየር ትራንስፖርት ኤጀንሲ የዶሞዴዶቮ፣ ሼሬሜትዬቮ እና ዡኮቭስኪ አውሮፕላን ማረፊያዎች ቢያንስ 36 በረራዎችን ማጠፋቸውን ፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ማረፊያዎቹ ስራቸውን መቀጠላቸውን አስታውቋል። በሞስኮ ቀጠና አንድ ሰው እንደተጓዳም ተነግሯል።
ሞስኮ እና ቀጠናው ቢያንስ 21 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት፣ ከኢስታንቡል ጋር የሚስተካከል ፣ አውሮፓ ውስጥ ካሉት ትላልቅ "ሜትሮፖሊታን" አካባቢዎች አንዱ ነው።
ሩሲያ በበኩሏ በአንድ ሌሊት 145 ሰው አልባ አይሮፕላኖችን እንዳስወነጨፈች ዩክሬን ተናግራለች። የኪየቭ አስተዳደር የአየር መከላከያዎቹ ከእነዚህ ውስጥ 62ቱን ማምከኑን አስታውቋል። በተጨማሪም ዩክሬን በሩሲያ ብራያንስክ ግዛት የጦር መሳሪያዎች ማከመቻ ላይ ጥቃት ማድረሷን አስታውቃለች። 14ሰው አልባ አውሮፕላኖች በክልሉ ተመተው መውደቃቸውም ተነግሯል።
የሞስኮ ጦር ከጦርነቱ መጀመሪያ ወዲህ ፈጣን ግስጋሴ ማሳየቱን እና ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ፣ ለ2 ዓመት ከግማሽ የዘለቀው የዩክሬን ጦርነት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እየደረሰ መሆኑን አንዳንድ ባለስልጣናት ይናገራሉ።
በጥር ወር ስልጣን የሚረከቡት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በ24 ሰአት ውስጥ በዩክሬን ሰላም ማምጣት እንደሚችሉ ቢናገሩም ይህን ለማድረግ እንዴት እንደሚችሉ ግን ጥቂት ዝርዝሮችን ብቻ አጋርተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ትራምፕን ( እንኳን ደስ ያለዎት!) ለማለት በደወሉበት ወቅት የቴስላ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የትራምፕ ደጋፊ የሆኑት ኢሎን ማስክ ጥሪውን መቀላቀላቸውን የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ማስክ ለዩክሬን መከላከያ ጥረት ወሳኝ የሆኑ የስታርሊንክ የሳተላይት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጠውን የስፔስ ኤክስ ባለቤት ናቸው (ሮይተርስ)።