በፓኪስታን ደቡብ ምዕራብ ባሎቺስታን ግዛት በተጓዦች በተጨናነቀው የባቡር ጣቢያ ውስጥ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰው የቦንብ ጥቃት ቢያንስ 26 ሰዎች ሲገደሉ ከ60 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገለጸ።
ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን የሆኑት መሀመድ ባሎክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በኩቴታ ግዛት ዋና ከተማ የተከሰተው ኃይለኛ ፍንዳታ የደረሰው "100 የሚጠጉ ሰዎች" ይገኙበት በነበረው የባቡሩ የተሳፋሪ መቆያ ስፍራ ነው፡፡
ከተገደሉትና ከቆሰሉት መካከል ቢያንስ ግማሽ ያህሉ የፓኪስታን ጦር ሰራዊት አባላት ሲሆኑ የጥቃቱም ቀዳሚ ኢላማ እንደነበሩም ፖሊስ እና የሆስፒታል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ጥቃቱ የደረሰበት ግዛት መንግስት ቃል አቀባይ ሻሂድ ሪንድ እንደተናገሩት ከተጎዱት መካከል ቢያንስ 10 ሰዎች “በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ናቸው” ብለዋል ።
የአማፂ ቡድን የሆነው የባሎክ የነጻነት ጦር፣ የፓኪስታን ወታደራዊ አባላትን ኢላማ አድርጓል ለተባለው ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በኩዌታ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት በማውገዝ “ከንጹሃን ዜጎች ግድያ ጀርባ ያሉትን ለመቅጣት ቃል ገብተዋል” ሲል ፅህፈት ቤታቸው ኢስላማባድ ውስጥ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት በግዛቲቱ ማስቱንግ ከተማ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ቢያንስ 9 ሰዎች ሲሞቱ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም ተማሪዎች ነበሩ። ጥቃቱ ያነጣጠረውም የፖሊዮ ክትባቶችን የሚሰጡ ሰራተኞችን በሚያጓጉዝ የፖሊስ መኪና ላይ ነበር።