የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ዛሬ እንዳስታወቀው የእስራኤል የአየር ጥቃት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ በአንድ ሌሊት 14 ፍልስጤማውያንን መግደሉን ሲገልጽ የእስራኤል ጦር በበኩሉ በሰሜዊ ግዛት በደርዘን የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን መግደሉን አስታውቋል፡፡
በደቡባዊ ካን ዩኒስ አካባቢ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን በሚኖሩብባቸው ድንኳኖች ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 9 ሰዎች መሞታቸውን የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃም ጉዳቱን አረጋግጦ 11 ሰዎች በጥቃቱ ቆስለው ወደ ናስር ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጿል።
በጋዛ ከተማ በአል-ቱፋህ ወረዳ “በሺህ ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች” መጠለያነት በሚያገለግለው ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ ሁለተኛ የአየር ጥቃትም ህጻናትን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሲገደሉ 22 ያህሉ መቁሰላቸውንም ቃል አቀባዩ ተግረዋል፡፡
በቅርብ ወራት ውስጥ የእስራኤል ጦር የፍልስጤም ታጣቂዎች መሽገውባቸዋል ያላቸውን በርካታ ወደ መጠለያ የተቀየሩ ትምህርት ቤቶችን እየደበደበ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ሰራዊቱ በሰሜን ጋዛ ጃባሊያ አካባቢ “በደርዘን የሚቆጠሩ አሸባሪዎችን” መግደሉን የገለፀ ሲሆን ሃማስ እንደገና እንዳይሰባሰብ ከአንድ ወር በላይ የአየር እና የምድር ዘመቻ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጿል፡፡
የእስራኤል ወታደሮች በግዛቱ ደቡብ ራፋህ በተባለው አካባቢ በርካታ ታጣቂዎችን መግደላቸውንም ጦሩ አክሎ ገልጿል።
ወታደሮቹ በአሁኑ ወቅት በሁለት ግንባር ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ ያለው የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ከሄዝቦላህ እና በጋዛ ከሀማስ ጋር እየተፋለሙ ይገኛሉ ብሏል። ሃማስ እና ሂዝቦላ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች በአሸባሪነት የተፈረጁ ናቸው፡፡