ጦርነት ጋዜጠኞችን የሚገድሉትን አካላት ተጠያቂነት አስቸጋሪ ያደርገዋል ተባለ

  • ቪኦኤ ዜና

አንዲት ሴት ሞስኮ ውስጥ በተገደለችው ሩሲያዊቷ ጋዜጠኛ አና ፖሊትኮቭስካያ ፎቶ ፊት አበቦችን ስታኖር ። (ፎቶ ፋይል)

ጋዜጠኞች ዒላማ ለተደረጉበት ግድያ ፍትህን ማስፈን በተለይ በጦርነት ጊዜ የበለጠ የተወሳሰበ ከባድ ስራ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ በዓለም ላይ "85 በመቶው የጋዜጠኞች ግድያ አሁንም መፍትሄ አላገኘም" ሲል ዩኔስኮ ቅዳሜ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።
እ.ኤ.አ. በ2013 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እኤአ ህዳር 2ን በጋዜጠኞች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ያለመከሰስ መብትን የማስቆም ዓለም አቀፍ ቀን ብሎ አውጇል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ወይም ሲፒጄ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆዲ ጊንስበርግ “በጋዜጠኞች ግድያ ላይ ያለመከሰስ መብት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የተለመደ እና በተለይም እየተካሄደ ያለ ግጭት ችግሩን ያባብሰዋል” ብለዋል፡፡
እኤአ ከ2006 ጀምሮ በጋዜጠኞች ላይ ለደረሱ ግድያዎች 85 ከመቶ የሚሆኑት መፍትሄ ያላገኙ መሆናቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
እንደ እስራኤል-ጋዛ፣ ዩክሬን፣ ምያንማር እና ሄይቲ ያሉ ጦርነት እና ግጭቶች በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ይጨምራሉ፣ ምርመራዎችን እና የህግ ተጠያቂነትንም ያወሳስባሉ ተብሏል፡፡
በጋዛ 134፣ ባብዛኛው ፍልስጤማውያን የሆኑ ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፣ እስራኤል ተጠያቂነት በማጣት ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዘገባው አመልክቷል። እ.ኤ.አ. ጥቅምት 13 ቀን 2023 የሊባኖሱ የሮይተርስ ጋዜጠኛ ኢሳም አብደላህ የተገደለ ሲሆን ሌሎች 6 ጋዜጠኞችም ቆስለዋል፡፡
ዩክሬን ውስጥ ያለው የሩሲያ ጦርነት ቢያንስ 15 ጋዜጠኞች እንዲሞቱ አድርጓል፡፡
ዩኔስኮ እንደዘገበው በየአራት ቀኑ አንድ ጋዜጠኛ እንደሚሞት ገልጾ እነዚህን በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ወንጀሎች ለመግታት የፕሬስ ነጻነት ማስከበርና ህጋዊ እምርጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡