የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 11 ፓርቲዎችን በጊዜያዊነት አገደ

  • ቪኦኤ ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "በጠቅላላ ጉባኤ፣ በኦዲት እና በሴት አባላት አማካኝነት ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ጋራ በተያያዘ፣ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጊዜያውነት ማገዱን ትላንት ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፈው እና በፌስቡክ ገጹ ይፋ ባደረገው ደብዳቤ አስታውቋል።

ቦርዱ የእግድ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጌዲኦ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የሐረዲ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኅብረት እና አገው ለፍትህና ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገኙበታል።

ፓርቲው እግዱን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት በጻፈው በዚሁ ደብዳቤ፣ ቦርዱ የተለየ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ፣ ፓርቲዎቹ ከማንኛውም ሕጋዊ እንቅስቃሴ ታቅበው እንዲቆዩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በመሆኑም የተዘረዘሩት ፓርቲዎች የተጣለባቸው የእግድ ውሳኔ እስከሚነሳ ድረስ፣ በማናቸውም የጋራ ምክር ቤቱ የሚያዘጋጃቸው ጉባኤዎች ላይ ሊገኙ፣ ሊመርጡ፣ ሊመረጡ ወይም በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ሊያገለግሉ እንደማይችሉ ቦርዱ ጨምሮ ገልጿል።

እስካሁን ስማቸው ከተጠቀሰው ፓርቲዎች በኩል የወጣ መግለጫም ሆነ የተሰጠ አስተያየት የለም።