ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኢትዮጵያ በጋሞ ዞን በሚገኘው የጫሞ ሓይቅ በደረሰ የጀልባ አደጋ ሕይወታቸው ካለፈው 13 ሰዎች ውስጥ የአስራ ሁለቱን አስከሬን ማግኘታቸውን የካባቢው ባለሥልታናት አስታውቀዋል።
ባለፈው ሐሙስ አደጋው ሲደርስ ጀልባው 16 ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር ያስታውቀው የአካባቢው አስተዳደር፣ ሶስት ሰዎችን ወዲያውኑ ከአደጋው መታደግ እንደተቻለ ገልጿል።
የጀልባዋ ተሳፋሪዎችም “የቀን ሠራተኞች” እንደሆኑ ተገልጿል።
የዞኑ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ኮማንደር ረታ ተክሉ ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ ክፍል እንደተናገሩት፣ ጀልባው ቆሬ ዞን ከሚገኘው አቡሎ አርፊቾ አውራጃ ወደ ዞኑ መዲና አርባምንጭ በመጓዝ ላይ ነበር።