በፓሪስ በሚካሄደው ወታደራዊ የባህር ኃይል የንግድ ትርዒት ላይ የእስራኤል ተቋማት እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን ተከትሎ፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ፣ መስሪያቤታቸው በፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ላይ ክስ እንዲመሰርቱ ማዘዛቸውን እሁድ እለት አስታውቀዋል።
የእስራኤል ተቋማትን የማገድ ውሳኔው፣ እስራኤል በጋዛ እና ሊባኖን እያካሄደችው ባለው ጦርነት ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የሄደው የማክሮን መንግስት ቅሬታ አካል ነው።
እ.አ.አ ከህዳር 4 -7 በፓሪስ የሚካሄደው የባህር ኃይል የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ኢዩሮናቫል ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ የፈረንሳይ መንግስት፣ የእስራኤል ልዑካን በትርዒቱ ላይ መሳተፍም ሆነ መሳሪያዎቻቸውን ማሳየት እንደማይችሉ ማሳወቁን አመልክቷል። ውሳኔው ሰባት ተቋማት ላይ ተፅእኖ ማሳደሩንም ጠቅሷል።
ውሳኔውን ተከትሎ ካትዝ በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈረው መልዕክት "የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት፣ በመጪው ወር ፓሪስ ላይ በሚካሄደው የባህር ኃይል የንግድ ትርዒት ላይ የእስራኤል ተቋማት ምርቶቻቸውን እንዳያሳዩ በመከልከላቸው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሕጋዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንዲወስድ መመሪያ ሰጥቻለሁ" ብለዋል።
ካትዝ አክለው "ለሁለተኛ ጊዜ በእስራኤል ተቋማት ላይ የተጣለው እቀባም ሆነ ተቀባይነት የሌላቸው ቅድመ ሁኔታዎች ዲሞራሲያዊ ያልሆኑ ከመሆናቸውም በላይ፣ በሁለት ወዳጅ ሀገሮች መካከል ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው" ያሉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ማክሮን ውሳኔያቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዲሰርዙ አሳስበዋል።