ከስልጣናቸው የተባረሩት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ እሁድ እለት፣ አለቃቸውን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ "ጨካኝ" እና "አረመኔ" ሲሉ በመንቀፍ፣ ህይወታቸው አደጋ ላይ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ጋቻጉዋ ሐሙስ እለት በህግ መወሰኛ ምክርቤት ፊት ከተከሰሱባቸው 11 ክሶች አምስቱ ተቀባይነት በማግኘታቸው ከስልጣናቸው የተነሱ ሲሆን፣ በምትካቸው ሌላ የመሾሙን ሂደት ግን የፍርድ ቤት ውሳኔ አግዶታል።
"ፕሬዝዳንት እንዲሆን የረዳሁት፣ ያመንኩት እና እሱን በመደገፌ የተሳደድኩበት ሰው እንዴት በእኔ ላይ ይህን ላክል ጨካኝ ሊሆን እንደቻለ አስደንግጦኛል" ብለዋል ጋቻጉዋ።
የ59 ዓመቱ አዛውንት የተመደቡላቸው የፀጥታ አካላት መነሳታቸውን እና ሁሉም ሰራተኞቻቸው አስገዳጅ እረፍት እንዲወጡ መደረጋቸውንም ገልጸው "በእኔ ላይ ወይም በቤተሰቤ ላይ የሆነ ነገር ቢደርስ፣ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
ጋቻጉዋ ይህንን ንግግር ያደረጉት፣ በደረታቸው ላይ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ሲታከሙበት ከነበረው ሆስፒታል ከወጡ በኃላ ነው።
"ይህን አይነት መጠን ያለው ጭካኔ አይገባኝም" ያሉት ጋቻጉዋ "አንድ ሰው በህይወቱ እጅግ በጣም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ወቅት እና በህይወት ለመቆየት በሚፍጨረጨርበት ወቅት፣ ሆን ተብሎ እንደዚህ አይነት ጭካኔ ይፈፀምበታል" ብለዋል።