ተመድ ፣ እስራኤል በሰሜን ሊባኖስ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ዙሪያ ምርመራ እንዲካሄድ አሳሰበ

በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 15.2024 የተነሳው ምስል ፣ እስራኤል በሰሜን ሊባኖስ አይቶ መንደር ላይ የአየር ጥቃት ካደረሰች በኃላ ፣ ነዋሪዎች ፍርስራሽ ሲያጸዱ ፣ የሊባኖስ ጦር ወታደሮች ከጎናቸው ቆመው ያሳያል።

በሰሜን ሊባኖስ ቢያንስ 22 ሰዎችን በገደለው የእስራኤል የአየር ጥቃት ላይ ምርመራ እንዲካሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ዛሬ ማክሰኞ ጥሪ አድርጓል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ ቃል አቀባይ ጄርሚ ሎሬንስ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በ"አይቶ" መንደር በሰኞ ዕለቱ ጥቃት ከተገደሉት መካከል 12 ሴቶች እና 2 ህጻናት እንደሚገኙበት ተቋማቸው መረጃዎች እንደደረሱት አስታውቀዋል።


"ጥቃት የደረሰበት ባለ አራት ፎቅ የመኖሪያ ህንጻ መሆኑን ተረድተናል ። እነዚህን ነገሮች በአእምሯችን ይዘን፣ የጦርነት ሕጎች፣ የልዩነት እና ተመጣጣኝነት መርሆዎችን ከሚመለከተው ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጋር በተያያዘ ተጨባጭ ስጋቶች አሉን " ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ፣ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል የተወነጨፉትን በርካታ ተተኮሾች የሀገሪቱ የአየር መቃወሚያ ባመከነበት አፍታ ፣ በሀይፋ ክልል የአደጋ ጊዜ ማንቂያ ደወል እንዲሰማ እንደተደረገ የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች ፣ በደቡብ ሊባኖስ በሚገኙ የሂዝቦላ ኢላማዎች ላይ ባደረሱት የአየር ድብደባ በርካታ ተዋጊዎችን እንደገደሉ ይፋ አድርገዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒጃሚን ኔትኒያሁ ሰኞ ዕለት ፣ " (እስራኤል) ቤሩትን ጨምሮ ፣ በሁሉም የሊባኖስ ክፍሎች ሂዝቦላህን ካለ ርህራሄ ትመታለች" ሲሉ ዝተዋል።

እስራኤል ፣ ኢራን ላይ የምትፈጽመው የአጸፋ ጥቃት ፣የነዳጅ ዘይት ወይም ኒውክሌር ተቋሞች ላይ ሳይሆን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንደሚሆን ኔታንያሁ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደተናገሩ ፣ የአሜሪካ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።

ባለስልጣናቱን የጠቀሱት ፣ዋሽንግተን ፖስት እና ዎል ስትሪት ጆርናል ትናንት ሰኞ አመሻሽ ላይ እንደዘገቡት ፣ ኔታንያሁ ይሄንን ቃል የገቡት ባለፈው ሳምንት በመሪዎች መካከል በተደረገ የስልክ ውይይት ላይ ነው።

የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ "የዩናይትድ ስቴትስን አስተያየት እናዳምጣለን ፣ ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔያችን የምናስተላልፈው ብሔራዊ ጥቅማችንን ላይ መሰረት አድርገን ይሆናል " ብሏል።

ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ያደረሰችው ፣በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል በተፈጠረው ግጭት መባባስን ተከትሎ ፣ በኢራን የሚደገፈው የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን መሪ ሀሰን ናስራላህ ላይ እስራኤል ለፈጸመችው ግድያ ምላሽ ነው ።

እስራኤል ለኢራን ጥቃት አጸፋ ለመስጠት የዛተች ሲሆን ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እስራኤልን ለመከላከል የአየር መቃዋሚያ ስርዓት እና ስርዓቱን የሚዘውሩ ወታደሮችን እንደምትልክ አስታውቃለች።

( ቪኦኤ በዚህ ዘገባ ውስጥ ከአሶሼትድ ፕሬስ፣ ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እና ከሮይተርስ የተገኙ ግብዓቶች ተጠቅሟል ።)