እስራኤል ጋዛ ውስጥ በሚገኝ መስጂድ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 19 ሰዎች ተገደሉ

በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 6 የተነሳው ምስል አንድ ሰው ዳሂዬ ቤሩት ውስጥ በእስራኤል የአየር ድብደባ በተመታ ህንጻ ፍርስራሽ መካከል አነስተኛ ሞተር ብስክሌት ሲያሽከረክር ያሳያል ።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሚገኝ መስጂድ ላይ እሁድ ማለዳ በፈጸመችው ጥቃት በትንሹ 19 ሰዎች መሞታቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ገለፁ ። ከኢራን- አጋር ታጣቂ ቡድኖች ጋር የምታደርገው ጦርነት እየተስፋፋ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት፣ እስራኤል በሰሜን ጋዛ እና በደቡባዊ ቤይሩት ላይ የምታደርገውን የቦምብ ድብደባም አጠናክራለች ።


በማዕከላዊ ዲር አል ባላህ ዋና ሆስፒታል አቅራቢያ በሚገኘው ጥቃት የተፈጸመበት መስጂድ ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ተጠልለው እንደነበር ተነግሯል ።በከተማዋ አቅራቢያ የተፈናቀሉ ሰዎች በተጠለሉባቸው ትምህርት ቤቶች ላይ በተፈፀመ ሌላ ጥቃት ተጨማሪ አራት ሰዎች ተገድለዋል።

የእስራኤል ጦር ሁለቱም ጥቃቶች ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ቢልም ማስረጃ ግን አላቀረበም ።

የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ በአል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል የሚገኙ አስከሬኖችን ቆጥሯል ። በመስጂዱ ላይ በደረሰው ጥቃት የሞቱት በሙሉ ወንዶች መሆናቸውን የሆስፒታሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሀማስ ጥቃት ከሰነዘረ ከአንድ አመት በኋላ አሁንም እስራኤል ከቡድኑ ጋር እየተፋለመች ሲሆን ፣ በሊባኖስ አቅጣጫ ከሂዝቦላህ ጋር ለመፋለም አዲስ ግንባር ከፍታለች።

ሂዝቦላ የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በድንበር አካባቢ ከእስራኤል ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲያደርግ ቆይቷል።ቴህራን ባለፈው ሳምንት በእስራኤል ላይ የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ እስራኤል ኢራንን ለማጥቃት ዝታለች።

እየሰፋ ያለው ግጭት ለእስራኤል ወሳኝ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ የምትሰጠው ዩናይትድ ስቴትስን እንዲሁም የአሜሪካን ኃይሎች የሚያስተናግዱ የዩናይትድ ስቴትስ አጋር የአረብ ሀገራትን ወደ ጦርነቱ እንዳያስገባ ስጋት አጭሯል።

ይህ በእንዲህ እያለ ፣ የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ በምትገኘው ጃባሊያ አዲስ የአየር እና የምድር ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።ጃባሊያ እስራኤል ከተመሰረተችበት የ1948ቱ ጦርነት ማግስት ጀምሮ የብዙ ሕዝብ መኖሪያ የሆነው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መገኛ ናት ።ዘገባው የአሶሼትድ ፕረስ ነው ።