ፕሬዝዳንት ባይደን እስራኤል ኢራን ላደረሰችው የሚሳኤል ጥቃት እንዴት ምላሽ እንደምትሰጥ እስካሁን አልወሰነችም አሉ

  • ቪኦኤ ዜና

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዋሽንግተን በሚገኘው በዋይት ሀውስ ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ መስከረም 24፣ 2017 ዓ.ም.

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትላንት ዓርብ እንደተናገሩት እስራኤል ኢራን ላደረሰችው የሚሳኤል ጥቃት እንዴት ምላሽ እንደምትሰጥ እስካሁን አልወሰነችም ብለዋል፡፡ የኢራን የነዳጅ ማውጫ ቦታዎችን ላለመምታት ማሰብ ይኖርባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ባይደን በዋይት ሀውስ መግለጫ ላይ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ውሳኒያቸውን ካሳወቁ በኋላ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት የኢራን ከፍተኛ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ በቴህራን በሚገኘው ታላቁ መስጊድ ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ በእስራኤል ላይ አገዛዙ ወደ ኋላ እንደማይል ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ ነው፡፡

ፕሬዘዳንት ባይደን "እስራኤላውያን ለደረሰባቸው አስከፊ ጥቃት ከኢራናውያን ብቻ ሳይሆን ከሂዝቦላህ እስከ ሁቲዎች ሁሉ ምላሽ የመስጠት ሙሉ መብት አላቸው። ግን እውነታው በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ላይ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው." ሲሉ ተናግረዋል፡፤

ማክሰኞ ምሽት ላይ ኢራን ወደ 200 የሚጠጉ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን በእስራኤል ላይ አስወንጭፋለች። የእስራኤል ጦር አብዛኞቹ ሚሳኤሎቹን በአሜሪካ የባህር ሃይሎች ጥምር ሃይል እርዳታ ማምከን መቻሉንም አስታውቋል፡፡