እስራኤል ሊባኖስ ላይ የአየር ጥቃት ስታደርስ ሂዝቦላህ በድንበር ላይ ከወታደሮች ጋር ተዋግቷል 

እስራኤል በሊባኖስ ቤይሩት በዳሂህ አየር ድብደባ ካደረሰች በኋላ በአካባቢው ከፍተኛ ጭስ ታይቷል፣ መስከረም 25 2017 ዓ.ም.

ሂዝቦላ ተዋጊዎቹ በደቡባዊ ሊባኖስ ድንበር ላይ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር መዋጋታቸውን ገልጿል፡፡ በአንጻሩ የእስራኤል ጦር በመስጊድ ውስጥ የነበሩ በኢራን የሚደገፉትን የሂዝቦላ ታጣቂዎችን መምታቱን አስታውቋል፡፡

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ በበዳዊ የስደተኞች ካምፕ ላይ ዛሬ ቅዳሜ በደረሰውና “የፅዮናውያን የቦምብ ጥቃት'' ሲል በገለጸው የእስራኤል የአየር ጥቃት ሰኢድ አታላህ አሊ የተባለ ወታደራዊ አዛዡ ከባለቤቱና ሁለት ሴት ልጆቹ ጋር ተገድሏል ብሏል።

ሀማስ እአአ ጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ ያደረሰው ጥቃት አንደኛ አመት ሊይዝ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ኢራን በዚህ ሳምንት በእስራኤል ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት፣ሂዝቦላህ የሚተኩሳቸው ሮኬቶች እና እስከ የመን የደረሱት የኢራን አጋሮች ጥቃቶች ሁኔታው እንዲባባስ አድርገዋል፡፡

በሊባኖስ የሚገኙ ተፈናቃዮች ግን ጦርነቱ ቁሞ ወደ መኖርያቸው መመለስ እንደሚሹ እየገለጹ ነው፡፡

በቤይሩት መሀል ከተማ በግጭቱ ከተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት መካከል አንዱ የሆነው ኢብራሂም ናዝል “ጦርነቱ እንዲቆም እንፈልጋለን ወደ መኖርያችን እንድንመለስ እንፈልጋለን” ሲል ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግሯል፡፡

የእስራኤል ጦር እአአ ከመስከረም 23 ጅምሮ በሊባኖስ ዙሪያ በሂዝቦላህ ጠንካራ ይዞታዎች ላይ በከፈተው የተጠናከረ ጥቃት ከ1,110 በላይ ሰዎች መገደላቸውም ተገልጿል፡፡