መዲናዋን ሳና እና የሆዴዳን አየር ማረፊያ ጨምሮ በየመን በርካታ ሥፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈፀሙን በሁቲ አማፂያን ሥር የሚተዳደረው የአል ማሲራ ቴሌቪዥንና ነዋሪዎች አስታውቀዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ጥቃቱ በደቡብ የምትገኘውን የዳህማር ከተማንም ዒላማ ማድረጉ ታውቋል።
የአየር ጥቃቱ በአሜሪካና እንግሊዝ ኃይሎች እንደተፈጸመ የአል ማሲራ ቴሌቪዥን አስታውቋል። የእንግሊዝ መንግስት ግን በድብደባው እንዳልተሳተፈ ገልጿል።
የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ፣ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ከፍልስጤማውያን ጋራ ያላቸውን የትግል አንድነት ለማሳየት ካለፈው ህዳር ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ በሚተላለፉ ዓለም አቀፍ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰንዝሩ ሰንብተዋል።
የሁቲዎቹ ጥቃት የዓለም አቀፍ የመርከብ ዝውውርን ያስተጓጎለ ሲሆን፣ ከአሜሪካና እንግሊዝ የመልስ ጥቃት እንዲፈፀም አስገድዷል።
መርከቦችም በቀይ ባሕር እና ሱወዝ ካናል በኩል ማለፉን ትተው፣ በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ ለመዞር ተገደዋል።