ከአንድ ቀን በፊት በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገን በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አካባቢ ከደረሱት ሁለት ፍንዳታዎች ጋር በተያያዘ ሁለት ስዊድናዊ ታዳጊዎች መታሰራቸውን አሶሽዬትድ ፕሬስ አስታውቋል። ድርጊቱ ከሽብር ጥቃት ይያያዝ ወይም አይያዝ እንደሆን ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም የአቃቤ ሕግ ጠበቆች ተናግረዋል።
በርካታ የውጪ ዲፕሎማቶች በሚገኙበት አካባቢ ረቡዕ ጠዋት በደረሰው ፍንዳታ የተጎዳ ሰው ባይኖርም ፍንዳታውን ተከትሎ በአቅራቢያው የሚገኘው የአይሁድ ትምህርት ቤት ዛሬ ዝግ ሆኗል።
በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማንነታቸው እንዳይገለፅ የተደረጉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፣ ለ27 ቀናት በእስር እንዲቆዩ ሲታዘዝ፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ እና አምስት የእጅ ቦንቦችን በመያዝም የመጀመሪያ ደረጃ ክስ ቀርቦባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ሁለቱን ቦምቦች ኤምባሲው አጠገብ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ ከወረወሯቸው በኃላ መፈንዳታቸውን የአቃቤ ሕግ ጠበቃ ሶረን ሀርቦ ገልጸዋል።