የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር 100ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ዛሬ አክብረዋል። በዚህም የመጀመሪያው አንድ መቶ ዓመት ዕድሜ የቆዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነዋል።
ከእ.አ.አ 1977 እስከ 1981፣ 39ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉት ጂሚ ካርተር፣ ላለፉት አርባ ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ደግሞ ‘የካርተር ማዕከል’ ለተሰኘውና ከባለቤታቸው ሮዘሊን ካርተር ጋራ በመሆን ለመሠረቱት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሠርተዋል።
ሮዘሊን ካርተር በ96 ዓመታቸው ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ካርተር ላለፉት 19 ወራት የትውልድ ሥፍራቸው በሆነው ፕሌይንስ፣ ጆርጂያ በቤት ውስጥ እንክብካቤ በማግኘት ላይ ናቸው።
በዋይት ሃውስ ፊት ለፊት ባለው ሥፍራ ላይ “መልካም ልደት ለፕሬዝደንት ካርተር” የሚል ፅሑፍ ከ100 ቁጥር ጋራ በደማቁ ሰፍሯል።
ጂሚ ካርተር፤ ጊዜው ደርሶ የቀብር ሥና ሥርዓታቸው ሲፈፀም የወቅቱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ንግግር እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸዋል።
በእ.አ.አ 1976 ባይደን የደለዌር እንደራሴ በነበሩበት ጊዜ ለካርተር ፕሬዝደንታዊ እጩነት ድጋፋቸውን ገልፀው ነበር።