እስራኤል ሌላ ተጨማሪ የሄዝቦላ ከፍተኛ አመራር መግደሏን አስታወቀች

ቤሩት መስከረም 19/ 2017 ዓ.ም

እስራኤል የሄዝቦላው መሪ ሀሰን ናስረላህ ከተገደሉ ጥቂት ቀናት በኋላ ትላንት ቅዳሜ የቡድኑን ሌላ ከፍተኛ አመራር አባል መግደሏን ዛሬ አስታወቀች፡፡

በኢራን የሚደገፈው ታጣቂ ሄዝቦላህ ቡድን ከፍተኛ አመራር መግደሉን ያስታወቀው የሄዝቦላ መቀመጫ በሆነችው ሊባኖስ ላይ ጥቃቱን የቀጠለው የእስራኤል ጦር ነው፡፡

በጥቃቱ የተገደሉት የሄዝቦላህ ማዕከላዊ ምክር ቤት ዋና ሃላፊ የሆኑትን ናቢል ካዓውክ መሆናቸውን የእስራኤል ጦር በዛሬው መግለጫው አመልክቷል፡፡

እስራኤል የምትፈጽመውን ጥቃት ተክትሎ 250 ሺህ ሊባኖሳዊያን ወደ መጠለያ ሲገቡ 100 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ወዳጅ ዘመድ ጋር ተጠልለዋል ሲል የሊባኖስ መንግስት አስታውቋል።

የእስራኤሉ መሪ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ “የሽብረተኞች አርበኛ” ሲሉ የጠሯቸው የሄዝቦላው መሪ ሀሰን ናስረላህ ግድያ ውጥን ከአስር ዓመታት በላይ እንደፈጀ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የዋይት ኋውስ ብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በዚህ ሳምንት ከኤቢሲ የዜና ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ “እስራኤል ለሀገሯ እና ለህዝቧ ደህንነት ስጋት የሚሆኗትን የማስወገድ ሀላፊነት አለባት” ብለዋል፡፡

ጆን ኪርቢ አክለውም “በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ እኛም ውጥረቱን ለማርገብ አማራጭ መንገዶችን መፈለግ እንዳለብን እናንምናለን” ብለዋል።

እስራኤል ከናስረላህ እና ከሄዝቦላ አመራሮች በተጨማሪም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ምክትል መሪን ገድላለች።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የናስረላ ሞት “ሳይመለስ አይቀርም” በማለት የዛቱ ሲሆን ቴህራን አምስት የሀዘን ቀናት አውጃለች።

ተንታኞች ለናስረላህ ሞት እስራኤል ላይ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚኖር ቢስማሙም፤ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ እስራኤላዊያንም ዒላማ ሊደረጉ ይችላሉ እያሉ ነው።