የሂዝቦላ መሪ ተገደሉ 

ፋይል፡ የሊባኖሱ የሂዝቦላህ መሪ ሰይድ ሀሰን ናስራላህ በቤይሩት ከተማ አሹራ ለማክበር በተካሄደው ሀይማኖታዊ ስነስርዓት ላይ ለደጋፊዎቻቸውን ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ ኅዳር 4 2006 ዓ.ም. REUTERS/Khalil Hassan

የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላ መሪ ሃሰን ናስረላህን በቤሩት ባካሄደው የአየር ጥቃት መግደሉን የእስራኤል ጦር አስታወቀ፡፡

የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ናዳቭ በቀድሞ አጠራሩ ትዊተር ተብሎ በሚታወቀው የኤክስ ገጻቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ ነው የሃሰን ናስርላህን መገደል ያስታወቁት፡፡

ሌላው የእስራኤል ቃል አቀባይ ካፒቴን ዴቪድ አቭራሃም ትላንት ዓርብ በሊባኖስ ዋና ከተማ ላይ የተካሄደውን ጥቃት ተከትሎ የሂዝቦላ መሪ “ተወግዷል” ሲሉ ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሂዝቦላ ቅርብ የሆነ ምንጭ ከናስራላህ ጋር የነበረው ግንኙነት ከዓርብ ምሽት ጀምሮ 'ጠፍተዋል' ብሏል።

የእስራኤል ጦር የአየር ጥቃቱን ያደረሰው የሂዝቦላ አመራሮች በቤይሩት ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ዳሂህ ባለው ዋና መሥሪያ ቤታቸው በተሰበሰቡበት ወቅት መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሄዝቦላ የደቡብ ግንባር አዛዥ አሊ ካርኪን ጨምሮ ሌሎች የሂዝቦላህ አዛዦችም በጥቃቱ መገደላቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ዓርብ እለት በተፈጸመው ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲገደሉ 91 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል ፣ ስድስት አፓርታማዎችም ፈርሰዋል ብሏል፡፡

ሃሰን ናስራላህ ሂዝቦላን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ መርተዋል።

ዛሬ ቅዳሜ ሂዝቦላ ባወጣው መግለጫ የቡድን መሪው እና ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው ሀሰን ናስራላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደለቻውን አረጋግጧል።

ናስራላህ “ከሰማዕታት ጓደኞቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል” ብሏል በመግለጫው። ሄዝቦላህ “በጠላት ላይ የሚያደርገውን ቅዱስ ጦርነት እና ፍልስጤምን ለመደገፍ እንደሚቀጥል” ቃል ይገባል ብሏል።

እስራኤል ለሳምንታት በዘለቀው ከሂዝቦላህ ጋር ባደረገችው የተጠናከረ ውጊያ ሂዝቦላህን ከሶስት አስርት አመታት በላይ የመሩት ናስራላህ ግድያ ትልቁ ዒላማ ተደርጎ ተወስዷል፡፡