ፕሬዚዳንት ባይደንን ጠቅላይ ሚንስትር ስታርመር ዛሬ ይገናኛሉ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚንስትር ኬይር ስታርመር

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚንስትር ኬይር ስታርመር በዩክሬን ጉዳይ ለመነጋገር ዛሬ ዓርብ በዋይት ሀውስ ይገናኛሉ።
ሁለቱ መሪዎች የሚገናኙት ዩክሬን የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታኒያ ስሪት የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን በመጠቀም ወደ ሩስያ ዘልቃ በመግባት ኢላማዎችን መምታት በሚያስችሉ የጦር መሣሪያዎች አጠቀቃቀም ላይ የተጣሉ ገደቦች እንዲላሉላት የተጠናከረ ግፊት እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው፡፡
የመሪዎቹ ውይይት የሚካሄደው ዋይት ሀውስ የፖሊሲ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል የሚል ምልክት በታየበት ወቅት ቢሆንም መሪዎች ለውጦች መኖራቸውን ወዲያውኑ ያስታውቃሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
የዩክሬን ባለስልጣናት ጥያቄያቸውን በዚህ ሳምንት በኪቭ ጉብኝት ላደረጉት የዩናይትድ ስቴትስት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ላሚ በድጋሚ አቅርበዋል፡፡
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ሩሲያን በረዥም ርቀት መሳሪያ እንድትመታ መፍቀዱ ግጭቱን በቀጥታ ወደ ኔቶ እና ሩሲያ ጦርነትነት ሊያሸጋግረው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው የሩስያን አየር ማረፊያዎች መምታት የሚያስችሉ ልዩ የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን መጠቀም እንደሚፈልጉ መወትወቱን ቀጥለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የራሷን ቴክኖሎጂ ተጠቅማ በሩሲያ ውስጥ መምታት የቻለችው ዩክሬን የተባሉትን የረጅም ርቀት መሣሪያዎች ማግኝቷ የጦርነቱን ውጤት በወሳኝነት አይለውጡም ብለው ያምናሉ።
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር የዩክሬን ራሷን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ በድጋሚ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብሪታንያ ከሩሲያ ጋር ግጭት እንደማትፈልግ በአጽንዎት ተናግረዋል፡፡
የባይደን አስተዳደር ሩሲያ ከኢራን ጋር ያላት ወታደራዊ ግንኙነት በተለይም ኢራን ለሩሲያ የአጭር ርቀት ሚሳይል ማቅረቧ እንደሚያሳስበው አመልክቷል፡፡
የሁለቱ መሪዎች ውይይት በጋዛ ያለውን ሁኔታ እና ለመጪው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የዩናይትድ ስቴትስን እና ብሪታኒያን አቋም ለማስማማት ያለመ ነው፡፡

የሁለቱ መሪዎች ውይይት በጋዛ ያለውን ሁኔታ እና ለመጪው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የዩናይትድ ስቴትስን እና ብሪታኒያን አቋም ለማስማማት ያለመ ነው፡፡