በአሜሪካ የሴት ጓደኛውን ገድሎ ወደ ኬንያ ሸሽቷል የተባለ ግለሰብ ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠቱን የኬንያ አቃቢያነ ሕግ ዛሬ አስታውቀዋል።
ባለፈው ኅዳር ወር የሴት ጓደኛውን በባስተን ሎጋን አየር ማረፊያ መኪና ማቆሚያ ሥፍራ በስለት ወግቶ በመግደል ወደ ኬንያ ሸሽቷል የተባለው ተጠርጣሪ ኬቭን ካንጌቲ፣ በጥር ወር በቁጥጥር ሥር ቢውልም፣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ከናይሮቢ እስር ቤት በማምለጡ ለሶሶት ወራት ሲፈለግ ቆይቶ እንደገና ተይዞ ነበር። ክስተቱ የኬንያን ፖሊስ ያሳፈረ ነበር ተብሏል።
ኬቭን ካንጌቲ ትላንት እሁድ ወደ አሜሪካ መላኩን እና ነገ ማክሰኞ ባስተን በሚገኝ ፍ/ቤት በግድያ ወንጀል ክስ እንደሚቀርብበት የኬንያ አቃቢያን ሕግ ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው አሜሪካ ከሚገኘው የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ጋራ በመሆን ተጠርጣሪው በአስቸኳይ ለሕግ በሚቀርብበት ጉዳይ ላይ በትብብር እንደሰራም አስታውቋል።
ከኬቭን ካንጌቲ ከእስር ማምለጥ ጋራ በተያያዘ አራት የፖሊስ ዓባላትና ሁለት ዘመዶቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ታውቋል።
በኬንያ በርካታ ሴቶችን አካላቸውን ቆራርጦ በመግደል የተጠረጠረ ግለሰብም ከሳምንታት በፊት ከናይሮቢ እስር ቤት አምልጦ በመፈለግ ላይ ነው።