የሩስያ ባለስልጣናት ዩክሬን እሁድ ማለዳ ላይ በሞስኮ እና በቴቨር ክልሎች የኃይል እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎችን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ክልሎች ላይ ያነጣጠረ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጥቃት ማድረሷን ገለጹ ።
በመንግስት የሚተዳደረው ታስ የዜና ወኪል ፣ የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው ፣ የሀገሪቱ የአየር መከላከያ አውታሮች 158 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አውድመዋል። ሚኒስቴሩ በቴሌግራም እንዳስታወቀው ከዩክሬን ጋር በሚያዋስኑት የኩርስክ፣ ብራያንስክ፣ ቮሮኔዝ እና ቤልጎሮድ ክልሎች ቁጥራቸው 122 የሆኑ ድሮኖቹን ማርገፉን አስታውቋል።
ከሩስያ የተሰጡ መግለጫዎችን በተናጠል ማረጋገጥ አልተቻለም። በዩክሬን በኩልም የተሰጠ አስተያየት የለም።የአሁኑ ጥቃት የተፈጸመው ፣ ከ200 በላይ የሩስያ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ ፣ ከግዙፎች መካከል አንዱ መሆኑ የተነገረለት ጥቃት ከፈጸሙ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የሩስያ ወታደሮች በምስራቃዊ ዩክሬን በተለይም በዶኔትስክ አካባቢ እየገፉ እንደሆነ እየተነገረ ባለበት እና ዩክሬን በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ጥቃት በመሰንዘር ወደፊት መግፋታቸው ከተዘገበ አንድ ወር ሊሞላው በተቃረበበት ወቅት ነው የአሁኑ ጥቃት ዜና የተሰማው ።
ኪየቭ ሩሲያ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ለማጥቃት ትችል ዘንድ በአጋር መንግስታት በኩል በሚቀርቡ የጦር መሳሪያዎች ላይ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ ዋሽንግተንን ስታሳሰብ ቆይታለች። ዩክሬን እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች ሞስኮ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጥቃት ለመቀጠል ያላትን አቅም በእጅጉ ይጎዳል ትላለች።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ ተገኝተው ፣ ዘለንስኪ ሀገሪቱን "በእውነት እና ሙሉ በሙሉ" ለመጠበቅ አቅም ይሰጣል ላሉት ዕቅድ አሜሪካ እገዛ ተማጽነዋል።
ለሩሲያ የደህንነት አገልግሎት ቅርብ የሆነው ባዛ ቴሌግራም የዜና ጣቢያ እንደዘገበው እሑድ ማለዳ በቴቨር ክልል ውስጥ በሚገኘው የኮንኮቮ የኃይል ጣቢያ አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰምቷል ።
የክልሉ አስተዳዳሪ ኢጎር ሩዴኒያ እንደተናገሩት በቴቨር ክልል አምስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወድመዋል። የደረሰውን የጉዳት መጠን ግን አልጠቀሱም።
ሮይተርስ እንደዘገበው ከ10 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በቮሮኔዝ ክልል ወድመዋል፣ በርካቶች ደግሞ በኩርስክ፣ ሊፕትስክ፣ ራያዛን እና ቱላ ክልሎች "ወድመዋል" ሲሉ የነዚህ ክልሎች ገዥዎች ተናግረዋል።
በጥቃቱ ምክንያት ስለ ደረሰ ጉዳትም ሆነ ውድመት ይፋ የተደረገ መረጃ የለም ። ሩሲያ በዩክሬን የአየር ጥቃት የሚደርሱ ጉዳቶች ሙሉ ይዘት አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ይፋ አታደርግም ።