Your browser doesn’t support HTML5
ኮሜርሻል ኖሚኒስ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀጠራቸው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሊሰናበቱ እንደኾነ ተገለጸ፡፡
ከሥራ ይሰናበታሉ የተባሉት ሠራተኞችም፣ ከነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የሥራ ውላቸው እንደሚቋረጥ ኮሜርሻል ኖሚኒስ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደሰጣቸው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞቹ፥ “ለረዥም ጊዜ ከሠራንበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መብታችን ሳይከበር አላግባብ ከሥራ ልንወጣ አይገባም፤” ብለዋል፡፡
የኮሜርሻል ኖሚኒስ የሠራተኛ ማኅበር ደግሞ፣ ሰባት ሺሕ የሚገመቱ ሠራተኞች ሊሰናበቱ መኾናቸውን ገልጾ፣ “የሠራተኞቹ ጥያቄ በአግባቡ ካልተስተናገደ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እወስደዋለኹ፤” በማለት አስጠንቅቋል፡፡
የሚሰናበቱት ሠራኞች 7ሺ ሳይሆኑ 2ሺ 500 መሆኑን የገለጸው ኮሜርሻል ኖሚኒስ በበኩሉ፣ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደማይመለከት ጠቅሶ፣ “የባንኩ ሁለት የሥራ መደቦች በመታጠፋቸው፣ በቦታው ተመድበው ሲሠሩ የነበሩ 2ሺሕ500 ሠራተኞች የሥራ ውላቸው ይቋረጣል፤” ብሏል፡፡ እነዚኽን ሠራተኞች ወደ ሌሎች ደንበኞች ለማዛወር እየሠራ መኾኑንም ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቋል፡፡
ስለ ጉዳዩ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡