ፍልሰተኞችን የጫነ ጀልባ በየመን የባህር ዳርቻ መስጠሙን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን አሊያም መጥፋታቸውን የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ድርጅት በዛሬው ዕለት አስታወቀ ። አደጋው የበርካቶችን ህይወት ከቀጠፉ እና በተደጋጋሚ ከደረሱ የጀልባ መስጠም አደጋዎች የቅርብ ጊዜው ነው ።
በሰሜን ሳውዲ አረቢያ ፣ በሰሜን ምስራቅ ኦማን የምትጎራበታት የመን ለ10 ዓመታት የተቃረበ የእርስ በርስ ጦርነት እየተደረገባት ቢሆንም ፣ አሁንም ድረስ ከምስራቅ አፍሪካ ለሚነሱ እና ወደ በለጸጉት የባህረ ሰላጤው ሀገራት ለመድረስ ለሚጥሩ ስራ ፈላጊ ፍልሰተኞች ዋነኛ መሸጋገሪያ የጉዞ መስመር ሆና ተገለግላለች ።
በታይዝ ግዛት ጀልባው ለአደጋ በተዳረገበት ወቅት 25 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን እና ሁለት የመናዊ መረከብ ዘዋሪዎችን ጭኖ እንደነበረ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ተቋም (አይ ኦ ኤም) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። እስካሁን ድረስ የ11ወንዶች እና 2 ሴቶች አስክሬን የኤደን ባህረሰላጤ እና ቀይ ባህርን በሚያገናኘው በባበል ኤል መንደብ መተላለፊያ ባህር ዳርቻ መገኘቱን እና ሁለቱን የመናዊያን ጨምሮ 14 ሰዎች የገቡበት እንዳልታወቀ ተገልጿል ። ፍልሰተኞች ከጂቡቲ የተነሱ እንደነበሩ አይ ኦ ኤም አስታውቋል ።
የ የመን የአይ ኦ ኤም ተጠባባቂ ሃላፊ ማት ሁበር “ይህ የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ ክስተት በዚህ መስመር ላይ ስደተኞች የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች የሚያሳይ ትልቅ ማስታወሻ ነው” ብለዋል።“በእነኝህ አደገኛ ውሃማ አካላት ውስጥ ያጣናቸው ነፍሶች ሁሉ በእጅጉ የበዙ ናቸው ።እኒህን አስከፊ የህይወት ቅጥፈቶች እንደተለመደ ክስተት ልንቆጥራቸው አለመሻታችን ቁልፍ ጉዳይ ነው " ሲሉም አክለዋል ።
እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየመን የሚደርሱት ስደተኞች በሦስት እጥፍ አድጓል ። በ2021 እኤአ ፣ 27,000 ገደማ የነበረው የፍልሰተኞች ቁጥር ባለፈው አመት ከ97,200 በላይ መድረሱን አይ ኦ ኤም የገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 380,000 የሚጠጉ ስደተኞች ግጭት ባየለባት ሀገር ውስጥ ይገኛሉ።
የመን ለመድረስ ፣ፍልሰተኞቹ ቀይ ባህርን ወይም በኤደን ባህረ ሰላጤ ለማቋረጥ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት አደገኛ በሆኑና በተጨናነቁ ጀልባዎች ይወሰዳሉ። ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 2,082 ስደተኞች የገቡበት አልታወቀም ፣ ከእነዚህም መካከል 693 ያህሉ ሰጥመው መቅረታቸውን አይ ኦ ኤም ይናገራል ።
በሰኔ ወር ቢያንስ 49 ስደተኞች በየመን ደቡባዊ የባህር ዳርቻ ጀልባቸው በመስጠሙ ሞተዋል።140 ሰዎች ደግሞ የገቡበት እንዳልታወቀ ድርጅቱ አስታውሷል።ተጨማሪ 62 ስደተኞች ባለፈው ሚያዝያ ወር የመን ለመድረስ ሲሞክሩ በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ላይ በተከሰቱት ሁለት የጀልባ መገልበጥ አደጋዎች ህይወታቸው አልፏል።