በእስራኤል ጥቃት ከ30 በላይ ፍልስጤማውያን ተገደሉ

  • ቪኦኤ ዜና
ትላንት ዓርብ እ.ኤ.አ. ነሀሴ 23 ቀን 2024 በእስራኤል ጦር የተለቀቀው ይህ ምስል የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ሲንቀሳቀሱ ያሳያል

ትላንት ዓርብ እ.ኤ.አ. ነሀሴ 23 ቀን 2024 በእስራኤል ጦር የተለቀቀው ይህ ምስል የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ሲንቀሳቀሱ ያሳያል

በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ እስራኤል ዛሬ ቅዳሜ በፈጸመችው በርካታ የአየር ድብደባ ቢያንስ ከ30 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

ፍልስጤማውያኑ የተገደሉት ግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተያዘው የተኩስ አቁም ንግግር ዝግጅት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው፡፡

ካን ዮኒስ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ በደረሰ የአየር ድብደባ ከሞቱት መካከል ሁለት ህጻናትን ጨምሮ 11 የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ ይገኙበታል።

ናስር ሆስፒታል በካን ዩኒስ እና አካባቢው በተደረጉ ሶስት ጥቃቶች የተገደሉ 33 አስከሬኖችን ማግኘቱን የገለፀ ሲሆን አል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል ሌላ ሶስት አስከሬን ተቀብሏል፡፡

ከካን ዮኒስ በስተደቡብ ባለው መንገድ ላይ በተፈጸመው የአየር ድብደባ ባጃጅ (ቱክ-ቱክ) ተሳፋሪዎችን እና በአካባቢው የነበሩ መንገደኞችን ጨምሮ፣ 17 ሰዎች ተገድለዋል፡፡

በከካን ዮኒስ በስተምስራቅ በሚገኝ ሌላ ስፍራ በተካሄደ ጥቃት እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የነበሩ በትንሹ አምስት ሰዎች መገደላቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

"ሪፖርቶቹን ገና እየተመለከትኩ ነው" ያለውን የእስራኤል ጦር አስተያየት ወዲያውኑ ማግኘት አለመቻሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡