የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በግጭት የተጎዱትን ለመርዳት በሁለት ቁልፍ መንገዶች ደህንነቱ የተጠበቀ የሰብአዊ አገልግሎት መተላለፊያ እንዲኖር መስማማታቸውን በስዊዘርላንድ ድርድር የተሳተፉ ሀገራት ዛሬ አርብ አስታወቁ።
በሱዳን ያለውን ስቃይ ለማርገብ እና ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም እንዲኖር ለማድረግ እኤአ ከነሀሴ 14 ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ የተመሩ ውይይቶች በስዊዘርላንድ ተካሂደዋል።
የፈጥኖ ደራሹ ጦር በውይይቱ ቢሳተፍም በአካል ያልተኙት የሱዳን ጦር ሃይሎች ከአደራዳሪዎች ጋር በስልክ መገናኘታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ዛሬ አርብ የተጠናቀቀው ውይይት በሳኡዲ አረብያ፣ ስዊዘርላንድ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተባበሪነት መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
በሱዳን ህይወት ለማዳን እና ሰላም እንዲወርድ የሚሰራው ቡድን የሰአብዊ ተደራሽነት እንዲኖር ሁለት ቁልፍ አካባቢዎች እንዲከፈቱ ከተፋላሚ ወገኖች ጋር ስምምነት ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
አካባቢዎቹ አንደኛው በምዕራብ ሱዳን ድንበር በዳርፉር ውስጥ አድሬ ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን ሌላኛው በሰሜን እና ከፖርት ሱዳን በስተደቡብ ያለው የዶሃ መንገድ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እኤአ ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በአብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር እና በመሀመድ ሀምዳን ዳግሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች እየተዋጉ ነው፡፡
ጦርነቱ በዓለም ላይ ካሉት አስከፊ ሰብአዊ ቀውሶች አንዱን አስከትሏል።