አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የዴሞክራቶች ጉባኤ የዩናይድ ስቴትሷ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ ታሪካዊ በሆነ ሂደት በፕሬዝዳንታዊው የምርጫ ፉክክር የፓርቲያቸው እጩ ሆነው የተሰየሙበትን ውሳኔ በሚቀበሉበት ሥነ ስርአት ዛሬ ምሽት ይጠናቀቃል።
በሥነ ስርአቱም ሃሪስ ለሃገራቸው ያላቸውን ራዕይ ይፋ በማድረግ፤ ከሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ የተሻሉ አማራጭ የሚሆኑበትን ምክኒያት ያሳያሉ።
በዚህም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዳግም ምርጫ ዘመቻ አክትሞ በምትካቸው ሃሪስ የዲሞክራት ፓርቲያቸው ፕሬዝዳንታዊ እጩ እንዲሆኑ ድጋፋቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ወሩን ሲታይ ለነበረው አጀብ የበዛው እንቅስቃሴም ማብቂያ የሚያበጅ ይሆናል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የዘመቻ ባለሥልጣን እንደገለፁት ሃሪስ ምሽቱ ላይ በሚያሰሙት ንግግራቸው ሦስት ጉዳዮችን እውን የማድረግ አላማ አላቸው።
መካከለኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ የወጡበትን ታሪካቸውን፣ ለሃገራቸው ያላቸውን “ብሩህ” ራዕይ እና “ጸለምተኛ” ካሉት የትራምፕ አጀንዳ ጋር በማነፃፀር እንደሚያሳዩ ይህም የሀገር ፍቅር ስሜትን እንደሚቀሰቅስ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
መድረኩ የፊታችን ጥቅምት ወር መገባደጂያ ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሃሪስ የአያሌ ሚሊዮን መራጮች ቀልብ ለማግኘት ካሏቸው ዕድሎች አንዱ ነው።