የቀድሞው የኤርትራ የገንዘብ ሚንስትር በእስር ላይ ሳሉ አረፉ 

  • ቪኦኤ ዜና
የቀድሞ የኤርትራ ፋይናንስ ሚንስትር ብርሃነ አብርኸ

የቀድሞ የኤርትራ ፋይናንስ ሚንስትር ብርሃነ አብርኸ

የቀድሞው የኤርትራ የገንዘብ ሚንስትር ብርሃነ አብርኸ ከመስከረም 7, 2011 ዓም አንስቶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ባሉበት ህይወታቸው ማለፉን ለአሜሪካ ድምጽ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት የተናገሩ የቤተሰባቸው አባላት አረጋግጠዋል። አቶ ብርሃኔ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ጠያቂ አያገኛቸውም ነበር።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2001 እስከ 2012 የኤርትራ የቀድሞው የገንዘብ ሚንስትር የነበሩት አቶ ብርሃነ የመንግስትን ፖሊሲ በግልጽ የሚተቹ ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍት በውጭ አገር ካሳተሙ በኋላ ነው በኤርትራ የጸጥታ ባለሥልጣናት ተይዘው የተወሰዱት።

አቶ ብርሃነ በጸጥታ ባለስልጣናቱ ተይዘው ወደ እስር ቤት ከመወሰዳቸው አስቀድሞ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከስልጣን እንዲወርዱ እና አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚሉ ጥያቄዎችን በይፋ አሰምተው ነበር።

አገር ውስጥ ያሉ የቤተሰባቸው አባላት የህልፈታቸው ዜና በፖሊስ ቢነገራቸውም የኤርትራ መንግስት ግን በበኩሉ ይፋ መግለጫ አልሰጠም።

አቶ ብርሃነ ያሉበትን አስመልክቶ ካሁን ቀደም በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥያቄ የቀረበላቸው የኤርትራ ባለስልጣናት በሙሉ በተመሳሳይ አቶ ብርሃነ ያሉበትን ይፋ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።