ለሁለት ከተከፈለው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) አመራር አንዱን ቡድን የሚመሩት ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ልዩነቱ ይፋ ከኾነ በኋላ ፓርቲው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያለውን ውክልና ዳግም ለማደራጀት ፍላጎት እንዳለው ጠቁመው፣ በጉዳዩ ላይ፣ “ከፌደራል መንግሥት እና የክልሉን አስተዳደር ከመሠረቱ አካላት ጋራ ውይይት እናካሒዳለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ባልሰጠውና አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተቃውሞ ባልተሳተፉበት ጉባኤ፣ ዳግም የህወሓት ሊቀ መንበር ኾነው የተመረጡት ዶክተር ደብረ ጽዮን፣ ዛሬ ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ “በጉባኤው ህወሓትን ለማዳን የሚያስችል ሥራ ተፈጽሟል፤” ብለዋል፡፡
የጉባኤውን መካሔድ የተቃወሙ አመራሮች፣ “ወደ ጉባኤው ገብተው ሓሳብ እንዲሰጡ ተጠርተው አልቀረቡም፤” ያሉት ዶክተር ደብረ ጽዮን፣ “ከነዚኸ ሰዎች ጋራ በተለያየንበት ኹኔታ በቀጣይ ለሕዝባችን በየፊናችን እንዴት እንደምንሠራ ለመወያየት እንችላለን፤” ሲሉ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከቆመ በኋላ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው፣ በህወሓት እና በፌደራል መንግሥት ውይይት ነው፡፡ በጉባኤያችሁ ፕሬዚዳንቱን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በአስተዳደሩ የሚሠሩ የህወሓት አመራሮችን ከአባልነት አግዳችኋል፤ በዚኽ ኹኔታ ውስጥ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ጉዳይ የምትሠሩት ሥራ አለ ወይ? ተብለው በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት ዶክተር ደብረ ጽዮን፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ በችኮላ ሰው ለመተካት እንደማይሠሩ አመልክተዋል፡፡
ዶክተር ደብረ ጽዮን፣ ህወሓት፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ በተመለከተ፣ ከፌደራል መንግሥት፣ ከክልሉ የጸጥታ ኀይሎች እንዲሁም ከምሁራንና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ በብቸኝነት እየተሳተፈ ካለው ተቃዋሚው ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ ፓርቲ ጋራ እንደሚወያዩ ጠቁመዋል፡፡
በጉባኤው፣ ከፓርቲው ሓላፊነት እና አባልነት የታገዱ አመራሮች፣ ከእንግዲህ ህወሓትን እንደማይወክሉም ዶክተር ደብረ ጽዮን መናገራቸውን፣ ሙሉጌታ ኣጽብሓ ከመቐለ ዘግቧል፡፡