የማሊ ወታደራዊ ሁንታ የወቅቱን ፕሬዚደንት ከስልጣን አስወግደው ስልጣን ከያዙ ከአራት አመታት በኋላ የበዙ ማሊያውያን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተባባሱ መምጣቱን እና የማያቋርጥ የኃይል መቆራረጥ የንግድ ድርጅቶቻቸውን እየጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር እኤአ ነሀሴ 2020 በቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ በሚደገፉ ሙሰኛ ገዥዎች፣ በተስፋፋው የጂሃዲስት ዓመፅ እና የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የተቀሰቀሰውን የህዝብ ቁጣ ተከትሎ ነበር መፈንቅለ መንግስቱ የተካሄደው።
በማሊ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ በሚገኙት ቡርኪናፋሶና ኒጀርን ጨምሮ በሳህል ቀጠናዎች ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግስቶች ተካሂደዋል፡፡
ብዙዎች ማሊያውያን አሁንም ሕይወት እንዲሻሻል እየጠበቁ ናቸው፡፡ በእንጨት የሚስሩ የቤት ወስጥ እቃዎችን በማምረት የሚተዳደረው ኦማር ዲያራ ለሮይተርስ "የኤሌክትሪክ ሁኔታን የያዙበት መንገድ ችግር ነው። ብዙ ማሊውያን ከፍተኛ ኪሳራ እያጋጠማቸው ነው።" ሲል ተናግሯል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2021 በሁለተኛው መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠሩት የማሊ የወቅቱ ወታደራዊ ገዥዎች በየካቲት ወር ምርጫ ለማድረግ የገቡትን ቃል በማጠፍ በቴክኒካል ምክንያቶች ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመውታል፡፡
የዓለም ባንክ የከፋ የድህነት መጠን እየጨመረ ባለባት ማሊ ያለው የኢኮኖሚ እድገት ካለፈው አመት 3.5 በመቶ በዚህ አመት ወደ 3.1 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከማሊ ህዝብ 90 በመቶ የሚሆነው በድህነት ውስጥ ይኖራል።