እስራኤል ሁለት የሃማስ ከፍተኛ ታጣቂዎች መግደሏን አስታወቀች

እስራኤል፣ የጋዛ ሰርጥ እና ዌስት ባንክ

እስራኤል ትላንት ቅዳሜ በወሰደችው የአየር ጥቃት ሁለት የሃማስ ከፍተኛ ታጣቂዎች መግደሏን አስታውቃለች፡፡

እስራኤላውያንን በመግደል ተሳትፈዋል ያለቻቸው ከፍተኛ ታጣቂዎች በዌስት ባንክ ጄንኒን በተባለ ቦታ በመኪናቸው ውስጥ እንዳሉ መገደላቸውን ተገልጿል፡፡

የእስራኤል የደህንነት ተቋምና የመከላከያ ሃይሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ የተገድሉት ታጣቂዎች አህመድ አቡ አራ እና ራፊት ዳዋሲ እንደሚባሉ አስታውቀዋል፡፡

እስራኤል በመግለጫዋ ሁለቱ ታጣቂዎች በዌስት ባንክ ዮርዳኖስ ሸለቆ ውስጥ ዮናታን ዶይች የተባለ እስራኤላዊ የተገደለበት ጥቃት እቅድ ላይ የተሳተፉ ነበሩ ብላለች፡፡

ሃማስ በበኩሉ የተገደሉት ታጣቂዎች አድርሰውታል የተባለው ጥቃት ተፈናቅለው በጋዛ በሚገኙ ትምህርት ቤት በተጠለሉ ፍልስጤማውያን ላይ እስራኤል በፈጸመችውና 90 ሰዎች ሙተውበታል ለተባለው ጥቃት የተወሰደ የአፀፋ እርምጃ እንደሆነ አስታውቋል፡፡