ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ በመቐለ እያካሔደ በሚገኘው አወዛጋቢ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያልተገኙት የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት፣ በፓርቲው ስም እንዳይንቀሳቀሱ አገደ፡፡
ከታገዱት አመራሮች መካከል፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ ጉባኤ እያካሔዱ ያሉት የፓርቲው አመራሮች፣ “የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ናቸው፤ ካልቻሉም ግጭት መፈጠር የሚፈልጉ ናቸው፤” በማለት ወንጅለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የጉባኤው ቅድመ ዝግጅት የፓርቲውን አሠራር የጣሰ ሕገ ወጥ ነው፤ በማለት እንደማይሳተፉ አስቀድመው ይፋ ሲያደርጉ፣ የፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽንም ራሱን ከጉባኤው ማግለሉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች በክፍፍል ውስጥ ባሉበት ኹኔታ፣ ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረውና ዛሬ ቅዳሜ አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው 14ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በጉባኤው እንደማይሳተፉ ያስታወቁትን 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንና የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ከአመራርነት ማገዱን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ጉባኤ፣ ዛሬ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ጠቅላላ ጉባኤው ከተሠየመበት ዕለት ጀምሮ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ ሌላ ኃላፊነት እንደሌላቸው ገልጿል።
መግለጫው፣ በስም ያልጠቀሳቸው ከጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት፣ በጉባኤው እንደማይሳተፉ ፓርቲው የሰማው ከብዙኀን መገናኛ መኾኑን ጠቅሶ፣ ይህም “ከድርጅቱ ባህል እና አሠራር ውጪ ነው፤” ሲል ተችቷል፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ የተመረጡት፣ በ13ኛው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፣ በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት፣ አሁን እየተካሔደ ባለው ጉባኤ የሥልጣን ዘመናቸው እንደሚጠናቀቅ አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜም፣ “በፓርቲው ስም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም ኾነ የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን እንደሌለ ጉባኤው ወስኗል፤” ብሏል ህወሓት በዛሬው መግለጫው፡፡
በአንጻሩ፣ በጉባኤው እንደማይሳተፉ ቀደም ብለው ያስታወቁትና በዛሬው ውሳኔ ከታገዱት አመራሮች መካከል የኾኑት የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በዛሬው ዕለት ለክልሉ ብዙኀን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ጊዜም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴም ኾነ የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮምሽኑ ሕጋዊ ተቋማት ናቸው፤ ሲሉ የጉባኤውን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ፣ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ እውቅና የተሰጠው ህወሓት፣ አራት ሰዎች የፈረሙት እንጂ የፓርቲው ተቋማት የማያውቁት ነው፤ በማለትም አጣጥለውታል፡፡
አቶ ጌታቸው አያይዘውም፣ ጉባኤ እያካሔዱ ያሉት የፓርቲው አመራሮች፣ “የጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ናቸው፤ ካልቻሉ ግጭት መፈጠር የሚፈልጉ ናቸው፤” በማለት ወንጅለዋል፡፡
“ፍላጎታቸው ይህ መኾኑን አውቃለኹ፡፡ ከኹሉም በላይ ግን ከባባ ቢመጣም ወደ ግጭትም እንገባለን፤ የሚለው ግን ተቀባይነት የለውም፡፡ ከእነ እገሌ ተስማምተን እንሠራለን፤ እየተባለ ያለው ፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡ የትግራይ ክልል የጸጥታ ኀይሎች፣ የትግራይ ሉዓላዊነትን የማክበር ግዴታ አለባቸው እንጂ የሥልጣን ፍላጎት ላለው ደብረ ጽዮን ወይ ጌታቸው መሣርያ አይደሉም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ህወሓት እንዲድን ይፈልጋል፡፡ ይህ የሚኾነው ግን፣ ኹሉም አባላቱ እና ተቋማቱ የሚሳተፉበት ኹሉንም ዓይነት ዓቅም በመያዝና የትግራይን ቀጣይ ኹኔታ የሚያሳይ ሓሳብ ያለበት መድረክ ያስፈልገናል፡፡”ብለዋል፡፡
ለብዙኀን መገናኛ ዝግ ኾኖ የቀጠለው ይህ ጉባኤ፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው እንደኾነና ውሳኔዎቹም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ቦርዱ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡