ዩናይትድ ስቴትስ: ለኢትዮጵያ የ97 ሚሊዮን ዶላር ሰብአዊ ድጋፍ ይፋ አደረገች

Your browser doesn’t support HTML5

ዩናይትድ ስቴትስ: ለኢትዮጵያ የ97 ሚሊዮን ዶላር ሰብአዊ ድጋፍ ይፋ አደረገች

ለአፍሪካ 536 ሚሊዮን ዶላር ዐዲስ የሰብአዊ ድጋፍ ይፋ ያደረገችው ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከዚኽም 97 ሚሊዮን ዶላሩ ለኢትዮጵያ የተመደበ መኾኑን አስታውቃለች፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሲቪሎች ደኅንነት የዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ዑዝራ ዘያ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ፣ ዐዲሱን የዩናይትድ ስቴትስ የሰብአዊ ድጋፍ ፈንድ ይፋ አድርገዋል፡፡

“ዛሬ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ 536 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዐዲስ የሰብአዊ ድጋፍ ይፋ ሳደርግ ኩራት ይሰማኛል፤” ብለዋል ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡

ፈንዱ፣ በአፍሪካ የተቀባይ ማኅበረሰቦችን፣ ስደተኞችንና በግጭት የተጎዱ ሕዝቦችን ለመርዳት በስፍራዎቹ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡ ከጠቅላላው ድጋፍ ውስጥ 97 ሚሊዮን ዶላሩ፣ በኢትዮጵያ ላሉ የሰብአዊ ድጋፍ አጋሮች እንደሚሰጥ ያስታወቁት ዑዝራ፣ 87 ሚሊዮን የሚኾነው ደግሞ የስደተኞችን ፍላጎት ለማሟላት የሚውል ነው፤ ብለዋል፡፡

በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛዋ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ መኾኗን ዑዝራ አውስተው፣ ዛሬ ይፋ የተደረገውን ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ በዚኽ ዓመት ብቻ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት 3ነጥብ7 ቢሊዮን ዶላር የሰብአዊ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ከኬንያ ከተመለሱ በኋላ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና ከፍትሕ ሚኒስትሩ ዶር. ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ እንዲሁም ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ጋራ በሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ላይ መወያየታቸውንም ረዳት ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ፣ በአገሪቱ ሕዝብ እና የግዛት አንድነት፣ እንዲሁም ሉዓላዊነት ላይ ያላት አቋም የጸና መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑዝራ ዘያ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች ዩናይትድ ስቴትስን እንደሚያሳስቧትም በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል፡፡

በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ግጭት በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሣላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በኢትዮጵያ የቀጠሉ ግጭቶች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ “አሁንም ዩናይትድ ስቴትስን ያሳስባታል፤” ብለዋል፡፡

ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ዩናይትድ ስቴትስ ጥረት ማድረጓን እንደምትቀጥልና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ተጠያቂ እንዲኾኑ የሚያስችል ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ መጠየቋን እንደምትቀጥልም ገልጸዋል፡፡

ረዳት ሚኒስትሯ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት፣ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

“በኢትዮጵያ ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ጫናዎች ከባድ ናቸው፤ ከአበዳሪዎች፣ ለጋሾች እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ድጋፍ ሊሻሻሉ የሚችሉም አይደሉም፤” ያሉት ረዳት ሚኒስትሯ፣ በዋናነት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ኢትዮጵያውያን በሥራ ዕጦት እና በከፍተኛ የዋጋ ንረት እየተቸገሩ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአይኤምኤፍ ጋራ የደረሰበትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ስምምነት የሚያበረታቱትም ችግሩን እንደሚቀርፈው በማመን እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ “በአይኤምኤፍ የሚደገፈው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኢኮኖሚውን ምኅዳር እንዲሁም የግጭት መንሥኤዎችን፣ ድህነትንና ሥራ ዐጥነትን ለመቀነስ ይረዳል፤” ያሉት ዑዝራ፣ ይህም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን ሰፊውን ክልል ይጠቅማል ብለን እናምናለን፤ በማለት አክለዋል፡፡

በአንጻሩ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ በአጭር ጊዜ የዋጋ ንረትን ማባባስን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል፣ በርካታ የዘርፉ ባለሞያዎች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

መንግሥት በበኩሉ፣ የማሻሻያውን የሽግግር ወቅት እክሎች ለመቅረፍ፣ የደመወዝ ጭማሬ እና የተለያዩ ድጎማዎችን እንደሚያደርግ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡