በደቡብ ጎንደር ዞን የሦስት ወረዳዎች ነዋሪዎች በጎርፍ መከበባቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ካርታ

በደቡብ ጎንደር ዞን ሦስት ወረዳዎች፣ ከባድ ዝናም መጣሉን ተከትሎ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጎርፍ መከበባቸውን የገለጹ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ከ15ሺሕ በላይ ነዋሪዎች አስቸኳይ የነፍስ አድን ሥራ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል፡፡

የፎገራ እና የሊቦ ከምከም ወረዳ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለሞያዎች፣ ዛሬ ረቡዕ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ በሁለቱ ወረዳዎች በተለይ ከ12 በላይ የሚኾኑ ቀበሌዎች በጎርፍ መከበባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በቀበሌዎች ያሉ ስድስት ትምህርት ቤቶች እና ሁለት የእምነት ተቋማት፣ በጎርፉ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተናገሩት ባለሞያዎቹ፣ “በ3ነጥብ7 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ማሳ ወድሟል፤ በርካታ የቤት እንስሳትም በጎርፍ ተወስደዋል፤” ብለዋል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

በደቡብ ጎንደር ዞን የሦስት ወረዳዎች ነዋሪዎች በጎርፍ መከበባቸው ተገለጸ

የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ አስራደው፣ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን ወደ ሌላ ስፍራ ለመውሰድ፣ በአካባቢው ያለው የጸጥታው ችግር እና የበጀት እጥረት ዕንቅፋት እንደኾነባቸው ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው፣ “ችግሩ ከመከሠቱ በፊት ሰኔ ወር ላይ፣ ለሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል አስተዳደር አካላት ብናሳውቅም እስከ አሁን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፤” ብለዋል፡፡