ባለፈው ሚያዝያ ወር ከተገደሉት፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋራ በተያያዘ፣ ወንድማቸው ሚሎ ዑርጌሳን ጨምሮ በጸጥታ ኀይሎች የተያዙ ቢያንስ 11 ሰዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች ዛሬ ማክሰኞ ጠየቀ።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ያለአንዳች ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ እንዲለቅቁ የጠየቀው ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ የአቶ በቴን ግድያ በሚመለከት በሚያደርጉት ምርመራ ዓለም አቀፍ እገዛ እንዲጠይቁም አሳስቧል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች በመግለጫው፣ “አቶ በቴ ዑርጌሳ ለመጨረሻ ጊዜ በሕይወት የታዩት እ.አ. አ. ሚያዚያ 9 ቀን፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በምትገኘው የትውልድ ከተማቸው ባለች የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ነበር፤ በቀጣዩ ቀን ጠዋት በጥይት ጭንቅላታቸው ላይ የተመቱትንና እጃቸው ወደ ኋላ የታሰረውን የአቶ በቴን አስከሬን ነዋሪዎች በከተማዋ ዳርቻ ላይ አግኝተውታል፤” ብሏል።
ከዚያ በቀጠሉት ቀናት፣ የአካባቢው ፖሊስ፥ የአቶ በቴን ታናሽ ወንድም ሚሎን፣ የቤተሰባቸው ጓደኛ ኤባ ዋኔን፣ እንዲሁም አቶ በቴ የነበሩበትን የእንግዳ ማረፊያ ባለቤት ጨምሮ “በጠቅላላው 13 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል፤” ማለቱን መግለጫው ጠቅሶ፣ ብዙዎቹ አሁንም እንደታሰሩ መኾናቸውን አመልክቷል።
አቶ በቴ ዑርጌሳ፣ አቋማቸውን በድፍረት በመናገር የሚታወቁ የተቃዋሚው ኦነግ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እንደነበሩ መግለጫው አክሎ አውስቷል።
የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ክፍል ምክትል ዲሬክተር ሌቲሺያ ባደር፣ “የኢትዮጲያ ባለሥልጣናት፣ የተገደሉትን የተቃዋሚ መሪ ወንድም እና ሌሎቹንም ክስ ሳይመሠረትባቸው ማሰራቸው፣ ይበልጡን የሚያሳስባቸው ስለ አቶ በቴ ግድያ እውነቱ እንዲወጣ ሳይኾን እንዳይወጣ መከላከል መኾኑን የሚያሳይ ነው፤” ብለዋል። ሕግን ባልተከተለ መንገድ የታሰሩትን በሙሉ በአስቸኳይ መፍታትና ስለ ግድያው ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሔድ ዓለም አቀፍ እገዛ መጠየቅ አለባቸው፤” ሲሉም ለቲሺያ ባደር አስገንዝበዋል።
የአቶ በቴ አስከሬን በተገኘበት ማግስት፣ እጆቹ የኋሊት በቀበቶ የታሰረና ጭንቅላቱ ላይ በጥይት የተመታ ሰው አስከሬን፣ በደረቀ ወንዝ መፋሰሻ ጉድባ ውስጥ ተጥሎ የሚያሳይና የእርሳቸው አስከሬን እንደኾነ የተገለጸ ፎቶግራፍ፣ በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎች መዘዋወሩን፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኑ መግለጫ አውስቷል። በፌስቡክ የተሰራጨው ሌላው ፎቶግራፍ ደግሞ፣ “ከስፍራው የተለቀሙ ናቸው የተባሉ ስድስት የጠመንጃ ጥይት ቀለሆችን አሳይተዋል፤” ያለው ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ ፎቶግራፎቹ የተነሡበትን ቦታ እና ቀን ግን ለማረጋገጥ እንዳልቻለ አስታውቋል።
ይህንኑ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ የአቶ በቴ ዑርጌሳን ግድያ አውግዞ፣ “ለግድያው መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎች የሚዘዋወረው ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት የለውም፤” ማለቱን፣ የሰብአዊ መብቶች ቡድኑ መግለጫ ጠቅሷል።
የአቶ በቴ ወንድም አቶ ሚሎ ዑርጌሳ፣ “ግድያው በተፈጸመበት ቦታ አቅራቢያ የነበሩ የዐይን እማኞች፣ አስከሬኑን ሰዎች ‘ሬንጀር’ ከሚባለው የጸጥታ ኀይሎች ተሽከርካሪ ላይ ሲያወርዱ አይተናል፤” ማለታቸውን፣ መሠረቱን በዩናይትድ ስቴትስ ባደረገ የኦሮሞ ዳያስፖራ የዜና አውታር በቀረበ ቃለ መጠይቃቸው ተሰምቷል፤ ያለው መግለጫው፣ የአቶ በቴ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ በዚያኑ ዕለት መታሰራቸውንም አትቷል።