ከኢራን ጋራ ግንኙነት ያለውና በአሜሪካ ውስጥ የፖለቲካ ግድያ ለመፈጸም አሲሮ ነበር ያሉትን አንድ ፓኪስታናዊ ይዘው ክስ መመስረታቸውን በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኙ አቃቢያ ሕግ አስታውቀዋል።
አሲፍ መርቻንት የተባለው ግለሰብ ወደ ኒው ዮርክ በመምጣት ነፍሰ ገዳዮችንም ለመቅጠር ሞክሯል ተብሏል።
አሲፍ መርቻንት ግድያውን እንዲያከናውኑ የመረጣቸው ግለሰቦች ማንንነታቸውን የደበቁ የሕግ አስከባሪ አባላት መሆናቸውን እንዲሁም ቅድሚያ 5ሺሕ ዶላር እንደከፈላቸውም ታውቋል።
ግለሰቡ ተጨማሪ ትዕዛዝ ጠብቁ በማለት ከአሜሪካ ሊወጣ ሲል ተይዟል።
ግድያው በማን ላይ ሊፈጸም ታቅዶ እንደነበረ ለፍርድ ቤት የቀረበው ሰነድ አላመለከተም።
በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ ግድያ ለመፈጸም ከኢራን በኩል ዛቻ በመኖሩ ተጨማሪ ጥበቃ እንደተመደበ የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታውቀው ነበር። ባለፈው ወር በፔንሲልቬኒያ የተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ግን በቁጥጥር ሥር ከዋለው ግለሰብም ሆነ ከኢራን ዛቻ ጋራ እንደማይያያዝ ባለስልጣናት ጨምረው አስታውቀዋል።
ግለሰቡ ከፓኪስታን ወደ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊት በኢራን ለሁለት ሳምንታት እንደቆየ አቃቢያነ ሕግ ገልጸዋል።