ባለፈው ዓርብ አል-ሻባብ በሞቃዲሹ ባሕር ዳርቻ ላይ ያደረሰውን ጥቃት በመቃወም፣ በመቶ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ ከገለጹ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ መሪዎች አንዱ ሆነዋል።
በጥቃቱ 37 ሰዎች ሲሞቱ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዓርቡ የአል-ሻባብ ጥቃት ጋራ በተያያዘ፣ ቸልተኝነት ታይቶባቸዋል የተባሉ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በርካቶች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ አስታውቀዋል።
Your browser doesn’t support HTML5
መንግሥትም በባሕር ዳርቻው ላይ በመዝናናት ላይ በነበሩ ሲቪሎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንዳይፈጸም ማድረግ ነበረበት በሚል ትችት እየቀረበበት ይገኛል።
በቀጠናው የፀጥታ ተንታኝ የሆኑትና ባለፈው ሳምንት ሞቃዲሹ የነበሩት ሳሚራ ጌይድ እንደሚሉት፣ በአል-ሻባብ ላይ ይደረግ የነበረው ዘመቻ መቆሙ በሞቃዲሹ ቀላል ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸሙ ከፊል ምክንያት ነው ብለዋል።
“ይህን ጥቃት መመልከት ያለብን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበሩት ሁኔታዎች ጋራ አያይዘን መሆን አለበት።” ያሉት ሳሚራ ጌይድ “ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች አል-ሻባብን በመዲናዋ አቅራቢያ ባሉ ሥፍራዎች ላይ ከበባ ውስጥ ከተውታል። አል-ሻባብ በመዲናዋ ውስጥ ቦታ አልያዘም። እስከ አሁን ከከተማዋ ውጪ ያደርሱ የነበረው ጥቃት ተገቷል። እናም ወደ ከተማዋ በመግባት መንግስትንና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ኢላማ ማድረግ ሞከሩ።” ብለዋል።
ሳሚራ ጌይድ አክለውም፣ መንግሥት ሃገሪቱን ለማረጋጋት ጥረት በማድረግ ላይ ባለበት ወቅትም ቢሆን፣ አል-ሻባብ ሞቃዲሹን ማጥቃት እንደሚችል ማሳየት ይሻል ብለዋል።
Your browser doesn’t support HTML5
አክለውም፤ “ይህ ለሕዝብ ያሰራጩት መግለጫ ነው። ምንም የተቀየር ነገር እንደሌለና አል ሻባብ በቦታው እንዳለ ይገልጻል። እናም ሽብር እንደሚፈጽሙ ያስታውቃል።”ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ማውገዙ ቀጥሏል።
በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ መሪዎች ጥቃቱን በማውገዝ ቀዳሚ ሆነዋል። የጂቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ገሌ “በሲቪሎች ላይ ጥቃት መፈጸም የወንጀለኞቹን ተስፋ መቁረጥ ያሳያል” ብለዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በአሰቃቂው የሽብር ጥቃት የሰው ሕይወት በመጥፋቱና ጉዳት በመድረሱ ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶኛል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ መንግሥት ጋራ የባሕር በርን መጠቀም በተመለከተ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ፣ ከሶማሊያ መንግስት ጋራ ቅራኔ ውስት ገብታለች። ሁለቱ ወገኖች ለሌላ ዙር ውይይት ቱርክ ላይ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ/ም እንደሚገናኙ ይጠበቃል። አሸማጋይዋ ቱርክም ጥቃቱን አውግዛለች፡፡
በሶማሊያ የሰላም ልዑክ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያደረገችው ተሳትፎ፣ ሶማሊያን ለማረጋጋት ሃገሪቱ የከፈለችው መስዋትነት መሆኑን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በመናገር ላይ ናቸው።
”በዚህ አሳዛኝ ወቅት ተጎጂዎቹን፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም የስማሊያን ሕዝብ በፀሎት እናስባለን” ሲሉ አክለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ።
ከሶማሊያ ጋራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሌላት ኢራን ሳትቀር ጥቃቱን አውግዛለች፡፡
የኢራን የጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ጥቃቱን አውግዘው፣ ለሶማሊያ መንግስትና ለሰለባዎቹ ቤተሰቦች ሃዘናቸውን እንደገለጹ የሃገሪቱ የዜና አገልግሎት ኢርና አስታውቋል።