ዩናይትድ ስቴትስ በኒጀር አጋዴዝ የሚገኘውን የመጨረሻውን የጦር ሰፈር (ኤር ቤዝ 201) ለአካባቢው ባለስልጣናት አስረከበች።
የጸረ ሽብርተኝነት ጦር ስፈሩ በሀገሪቱ ከሚገኙ ሁለት ቁልፍ ወታደራዊ ጦር ስፈሮች አንደኛው መሆኑን የሀገር ውስጥ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የኒጀር መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ በጋራ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ ወታደሮች እኤአ እስከ መስከረም 15 ድረስ በቦታው መቆየት ይችላሉ።
ዛሬ በአጋዴዝ ከተማ የአየር ኃይል ጦር ሠፈር 201 የተደረገው ርክክብ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ወታደሮች በኒጀር ከተማ ኒያሜ የሚገኘውን መለስተኛ የሰው አልባ አውሮፕላን ጣቢያ ከለቀቁ በኋላ የተፈጸመ ነው፡፡
የኒጀር ወታደራዊ ገዥ የአሜሪካ ወታደሮች በሳህል ክልል የሚገኙ የአልቃይዳ እና የእስላማዊ መንግስት ቡድንን ለመዋጋት እንዲሰማሩ የሚያስችለውን ስምምነት ባላፈው መጋቢት ማብቃቱን አሳውቋል።
ኒጀር በሳህል ክልል የጂሃድ ዓመፅን በመቃወም ለምዕራባውያን ሀገሮች ቁልፍ አጋር ነበረች።
አሜሪካ እና ፈረንሣይ በቅርቡ በኒጀር ከ2,500 በላይ ወታደሮች የነበሯቸው ሲሆን ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ጋር በመሆን ለወታደራዊ እርዳታዎችና ሥልጠናዎች በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ አፍሰዋል፡፡