የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሁከተኞች ፈጣን የህግ ቅጣት እንደሚሰጥ ተናገሩ  

ፋይል፡ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ንግግር ሲያደርጉ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. (Henry Nicholls/Pool via REUTERS/File Photo)

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ዛሬ ሰኞ በተደረገ አስቸኳይ ስብሰባ በሶስት ህፃናት ግድያ ምክንያት የተቀሰቀሰውን የቀኝ አክራሪ እንግሊዛውያንን ብጥብጥ ተከትሎ ፈጣን የወንጀል ህግ ቅጣት እንደሚኖር ዛቱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የስኮትላንድ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ከሚኒስትሮች እና የፖሊስ አዛዦች፣ ጋር ባለፈው ማክሰኞ ሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ሁከት ለማስቆም በሚወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በነበረው ሁከት በርካታ ፖሊሶች የቆሰሉ ሲሆን፣ ሱቆች ተዘርፈዋል ንብረትም ወድሟል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ በሳምንቱ መጨረሻ ከ150 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ስታርመር መንግስት ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደውን ፈጣን ቅጣት ለማረጋገጥ እና የአካባቢ ኃይሎችን ለመደገፍ በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ መኮንኖችንና መደበኛውን ሠራዊት በማሰማራት "የወንጀል ፍትህን እንደሚያሳድጉ" አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋነኛው ትኩረቴ ይህን ስርዓት አልበኝነት ማስቆም ነው ብለዋል፡፡

ሁከቱ የጀመረው የቴይለር ስዊፍት ዘይቤ ላይ ተመስርቶ በሚሰጠው የዳንስ ትምህርት በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ አንድ ሰው ባደረሰው የስለት ጥቃት ሶስት አዳጊ ልጃገረዶች ከተገደሉና ሌሎች አምስት ደግሞ በጽኑ መቁሰላቸውን ከተነገረ በኋላ ነው፡፡

ጥቃቱንም ተከትሎ አጥቂው ጥገኝነት ጠያቂ ሙስሊም ነው የሚል የሀሰት ወሬ በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨቱ ነው፡፡

ፖሊስ ግን ተጠርጣሪው እዚያው እንግሊዝ ዌልስ ውስጥ የተወለደ የ17 ዓመት ወጣት መሆኑን አስታውቋል፡፡ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን የተጠርጣርው ወላጆች ከሩዋንዳ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ ከተገለጸም በኋላ ቢሆን አጥቂዎቹ መስጊዶችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ከመሰንዘር አላገዳቸውም፡፡

ሁከቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ፖሊስ በተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች ስደተኞችን በመቃወም አደባባይ ከወጡ ተቃዋሚዎችና ሁከት ፈጣሪዎች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስሯል፡፡

አመጸኞቹ እና የሙስሊም ቡድኖችን ጨምሮ እነሱን በመቃወም የወጡ የአመጽ ተሳታፊዎች ከፖሊሶች ጋር ግብግብ መፍጠራቸውም ተነግሯል፡፡

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ትላንት እሁድ በሁከትና ዝርፊያው የተሳተፉት በድርጊታቸው እንደሚጸጸቱ አስጠንቅቀዋል፡፡ ሁከቱን ተከትሎ የታየው አለመረጋጋት በ13 ዓመታት ውስጥ በእንግሊዝ የከፋው ሥርዓት አልበኝነት ነው ተብሏል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ ለወንጀልና ሁከቱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተነግሯል፡፡