በእስራኤል የጋዛ ጥቃት 18 ሰዎች ሞቱ - 2 እስራኤላውያን በስለት ተገደሉ

  • ቪኦኤ ዜና
ፍልስጤማውያን እስራኤል በጋዛ አልአቅሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኙ የመጠለያ ድንኳን አካባቢዎች ላይ እኤአ እሁድ ነሀሴ 4/ 2024 ባደረሰችው ጥቃት የተነሳውን ቃጠሎ ሲመለከቱ

ፍልስጤማውያን እስራኤል በጋዛ አልአቅሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኙ የመጠለያ ድንኳን አካባቢዎች ላይ እኤአ እሁድ ነሀሴ 4/ 2024 ባደረሰችው ጥቃት የተነሳውን ቃጠሎ ሲመለከቱ

እስራኤል ዛሬ እሁድ ማለዳው ላይ በጋዛ አል አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሰነዘረችው ጥቃት በድንኳን ተጥልለው የነበሩ አራት ተፈናቃይ ፍልስጤማውያንን ጨምሮ 18 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ቆስለዋል፡፡
የአል አቅሳ ሆስፒታል በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የተጠለሉበት በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኝ ዋነኛው የህክምና ተቋም ነው።
በሌላም በኩል ከቴል አቪቭ ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ አንድ ፍልስጤማዊ ሁለት ሰዎችን በስለት ወግቶ መግደሉን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ከእስራኤል የነፍስ አድን አገልግሎት ሜጋን ዴቪድ አዶም እንደተናገሩት በስለት የተወጉት በ70 ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ አንዲት ሴት እና የ 80 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ ሌሎች ሁለት ሰዎችም ቆስለዋል፡፡
የቆሰሉት ሰዎች በ500 ሜትር ልዩነት ሶስት ቦታዎች ላይ እንደነበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ አደጋውን ያደረሰው ፍልስጤማዊ መገደሉን አስታውቋል፡፡
በዲር አል-በላህ አካባቢ በተደረገ ሌላ የእስራኤል ጥቃት አንዲት ልጅ እና ወላጆቿ መገደላቸውን ሆስፒታሉ አስታውቋል።
በሰሜን ጋዛ የተፈጸመ ሌላኛው የእስራኤል ጥቃት ደግሞ አንድ መኖሪያ ቤት በማውደሙ በውስጡ የነበሩት ሶስት ህጻናት ወላጆቻቸው እና ሴት አያታቸውን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡
በጋዛ ከተማ አንድ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሶስት ሰዎች በተካሄደ ጥቃት ተገድለዋል ሲል በሃማስ የሚመራው የጋዛ ነፍስ አድን ተናግሯል፡፡
ትላንት ቅዳሜ በጋዛ ከተማ ወደ መጠለያ ጣቢያነት የተቀየረ አንድ ትምህርት ቤት በእስራኤል ጥቃት በመመታቱ ቢያንስ 16 ሰዎች መገደላቸውና 21 ሰዎች መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
"የፍስልጤማውያን ተዋጊዎች ሁል ጊዜ የሲቪል አካባቢዎችን በምሽግነት ይጠቀማሉ" ሲል የሚከሰው የእስራኤል ጦር፣ አካባቢዎቹ የሃማስ የጦር ማዘዣ ማዕከል ናቸው ብሏል፡፡
እስራኤል ሲቪሎችን ላለመጉዳት ጥረት እንደምታደርግ ብትናገርም፣ ሴቶችና ህጻናት ስለሚሞቱበትና በተናጥል ስለምታደርጋቸው ወታደራዊ ጥቃቶች ብዙ ጊዜ መግለጫ እንደማትሰጥ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የሐማስ ታጣቂዎች ባላፈው ጥቅምት ደቡብ እስራኤል ላይ በፈሙት ጥቃት አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ 1,200 የሚደርሱ ሰዎችን ገድለው 250 ታጋቾችን ወስደዋል፡፡
እስራኤል ከዚያን ጊዜ አንስቶ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ቢያንስ 39,500 ፍልስጤማውያንን መግደሏን የሰለማዊ ሰዎችና ታጣቂዎችን ለይቶ አላመለከተም የሚባለው የጋዛው ጤና ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡
በጋዛ ለ10 ወራት የዘለቀው ጦርነት እና በቅርቡ በሊባኖስ እና ኢራን ከፍተኛ ታጣቂዎች በተገደሉበት ወቅት ውጥረቱ ጨምሯል።
ኢራን እና አጋሮቿ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ በመግለጻቸው በአካባቢው ሌላ አውዳሚ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሯል።