የአሜሪካ ምክትል ፕሬዘዳንት ካማላ ሃሪስ የዲሞክራት ፓርቲ እጩ ለመሆን የሚያስችላቸውን ድጋፍ ከተሳታፊዎች ማግኘታቸውን የፓርቲው ብሄራዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ጃሚ ሃሪሰን ትላንት አርብ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ይፋ የሆነውም በበየነ መረብ የሚሰጠው የምርጫ ሂደት ከሚጠናቀቅበት መጭው ሰኞ አስቀድሞ ሲሆን ይህም ፕሬዘዳንት ባይደን በምርጫው እንደማይወዳደሩ ካሳወቁና ድጋፋቸውን ለሃሪስ ከሰጡ በኋላ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የተካሄዱ የምርጫ ቅስቀሳዎች ፍጥነትና ግለቱን ለማስጠበቅ ያላቸውን ጉጉት ያንጸባርቃል ተብሏል፡፡
ሃሪስ የመጀመርያ ጥቁር የፓርቲው እጩ ለመሆን የተዘጋጁ ሲሆን የዲሞክራት ፓርቲ እጩ ታሳቢ በመሆናቸው ክብር እንደተሰማቸውም ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህ ወር መጨረሻ በቺካጎ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ዴሞክራቶች በእርሳቸው ዙርያ በማሰባሰብ የፓርቲያችውን ጥንካሬ እንደሚያሳዩም ቃል ገብተዋል።
የዲሞክራት ብሄራዊ ኮሚቴ በበየነ መረብ ባካሄደው የገንዘብ ማሰባሰብያ ወቅት ሃሪስ ያገኙት ድጋፍ ቁጥርም ሆነ የትኞቹ ግዛቶች ድጋፋቸውን እንደሰጡ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡
እስካሁን ለእጩነት ሃሪስን ሊገዳድር የመጣ ሌላ እጩ የለም፡፡ ፕሬዘዳንት ባይደን ድጋፋቸውን ለምክትል ፕሬዘዳንቷ እንደሚሰጡ ከገለጡ በኋላ ካማላ ሃሪስ የዲሞክራት ድጋፍን በፍጥነት ማጠናከር ስለመቻላቸውም ተገልጿል፡፡