በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ የተገደሉት የሃማሱ መሪ ኢስማዬል ሃንዬ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ዓርብ በካታር ተፈጽሟል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ሀዘንተኞች ከቀብር በፊት በዶሃ ኢማም ሙሀመድ ኢብኑ አብዱል ወሃብ መስጂድ በተካሄደ የጸሎት ስነስርዓት ተገኝተዋል
ትላንት ሐሙስ በቴህራን ለሃኒዬ በተካሄደው ህዝባዊ የአስከሬን ሽኝት ስነ-ስርዓት ላይ በርካታ የሀዘንተኞች አክብሮታቸውን ሰጥተዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ እና አዲሱ ፕሬዚደንት ማሱድ ፔዚሽኪያን ተገኝተዋል፡፡
ሃኒዬ እና አንድ ጠባቂ ቴህራን ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉ ሲሆን የኢራን አብዮታዊ ዘብ እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል።
በሃማስ፣ በኢራን እና በሌሎችም በጥቃቱ የተከሰሰችው እስራኤል በቀጥታ የተናገረችው ነገር የለም።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኔ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ በግድያው ምክንያት “ከባድ ቅጣት” ይኖራል ሲሉ ዝተዋል።
ለግድያው ተጠያቂ የተደረገችው እስራኤል መሆኗ በክልሉ የከፋ ግጭት እንዳይቀሰቀስ አስግቷል፡፡
ግድያው የተካሄደው በቤይሩት የሂዝቦላህ አዛዥ ፉአድ ሹክርን የገደለውን የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ ነው።
ቱርክ እና ፓኪስታን ሃንዬ የተገደሉበትን የሐዘን ቀን ብለው ሲያውጁ ሐማስ ደግሞ "የቁጣ ቀን" ሲል ጠርቶታል።
ሀማስ የሃኒዬ ግድያ እና የጋዛ ጦርነትን በመቃወም ከጁምአ ሶላት በኋላ በመስጊዶች ተቃውሞ እንዲነሳ አሳስቧል
የፍስልጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን የፖለቲካ መሪ ሃኒዬ ከሌሎች የሃማስ ፖለቲካ መሪዎች ጋር መኖሪያቸው በካታር ዶሃ ነበር፡፡
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በሰሜን ካታር ከተማ ሉሳሊ ውስጥ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡ የአረብ እና የእስልምና መሪዎች፣ የፍልስጤም ቡድኖች እና ነዋሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡