በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች፣ የስልክ አገልግሎት ረዘም ላለ ጊዜ መቋረጡን የገለጹ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በኢኮኖሚያዊ እና የነፍስ አድን እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ተጽእኖ እያደረሰ መኾኑን ተናገሩ።
የአገልግሎቱ መቋረጥ ከአካባቢው የጸጥታ ችግር ጋራ ተዳምሮ፣ በከፍተኛ ኹኔታ እየተዛመተ ያለውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዳከበደውም ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ዞኖች በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች፣ የስልክ አገልግሎት ከሁለት ዓመታት በላይ ተቋርጧል።
የቄለም ወለጋ ዞን አንፍሎ ወረዳ ነዋሪ መኾናቸውን የገለጹትና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ግለሰብ፣ “ታጣቂዎች በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ” በሚል የስልክ አገልግሎቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት እንደተቋረጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዚኽም፣ በተለይ በምጥ ለሚያዙ ወላዶች የአምቡላንስ አገልግሎት ለመጥራት ስለማይችሉ፣ ለሰዓታት በእግር መጓዝን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን ለማስተናገድ መገደዳቸውን አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ የደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ወረዳ ነዋሪም፣ እርሳቸው በሚኖሩበት ወረዳ አገልግሎቱ ከተቋረጠ ዓመታት መቆጠራቸውን ጠቅሰው፣ ነዋሪው ስልክ ለመደወል ወደ ወረዳ ከተማዋ ግምቢ ድረስ ለመሔድ መገደዱን አስረድተዋል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
በዞኑ በርካታ ወረዳዎች “በወባ ወረርሽኝ ሥቃይ ውስጥ ናቸው፤” ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ መረጃውን ለሚመለከተው አካል አድርሰን መድኃኒት ለማግኘት ሁለት ቀናትን እንደሚወስድባቸው ገልጸዋል፡፡ “ታጣቂው በወረዳው አለ እየተባለ እንደ ሕዝብ መቀጣት አለብን?” ሲሉም ጠይቀው፣ መንግሥት የኅብረተሰቡን ችግር ተገንዝቦ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል።
ሌላው የቆንዳላ ወረዳ ነዋሪም፣ “ሕዝቡ ጨለማ ውስጥ እንዳለ ነው፤ ስለ ገበያ መረጃ የለውም፤ በሌላ አካባቢ ከሚኖሩ ቤተሰቦቹም ጋራ ለመገናኘት አይችልም፤” በማለት ችግሩን አብራርተው መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ባነሡት ቅሬታ ላይ፣ ከኢትዮ-ቴሌኮም ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።
ኾኖም፣ ድርጅቱ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ፣ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክልሎች ሥራ ያቆሙ 87 የሞባይል ጣቢያዎችን ጥገና እና አገልግሎት በተሳካ ኹኔታ ማደስ መቻሉን ገልጿል።
የጥገና እና አገልግሎት ዕድሳቱ፣ የምዕራብ እና የምሥራቅ ወለጋ፣ የሆሩ ጉዱሩ እና የቄለም ወለጋ ዞኖችን እንደሚጨምር ጠቅሶ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ነዋሪዎቹ ግን፣ አገልግሎቱ የተመለሰው፣ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ብቻ መኾኑን ይገልጻሉ። በአካባቢያቸው ያለው የቴሌፎን መሠረተ ልማት፣ በግጭቱ ምክንያት አለመጎዳቱንና የጥገና ሥራ እንደማይፈልግ ይናገራሉ። አገልግሎቱ የተቋረጠውም “በራሱ በመንግሥት ነው፤” ሲሉ ከሰዋል።