የውጪ ምንዛሬ ተመን በገበያ መወሰኑ “የዋጋ ንረትን ከማባባስ ያለፈ ዘላቂ እና መሠረታዊ ችግሮቻችንን የመፍታት ፋይዳ አይኖረውም፤” ሲል፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ/ኢዜማ/ ፓርቲ፣ ገበያ መሩን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ተቃውሟል፡፡
ኢዜማ፣ ትላንት ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በዚኽ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት “ለሚመጣው ማንኛውም ምስቅልቅል ውሳኔውን ያሳለፈው መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤” ብሏል፡፡
የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ ፀሓፊ ንጋቱ ወልዴ፣ “ወቅቱን ያልጠበቀ ነው” ያሉት ይህ ርምጃ፣ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዳ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ “የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን በቁንጽል ሳይኾን በምልአት መመልከት ይገባል፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “አካኼዳችን ድኻ ተኮር ነው፤ ትኩረታችንም ለችግር በመጠቃት ተጋላጭ የኾኑ ደካሞችን መደገፍ ነው፤” ብለዋል።
Your browser doesn’t support HTML5
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ሐምሌ 25 ቀን ከባለድርሻ አካላት ጋራ መወያየታቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡
“የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ የለውጥ ሥራውን ባልተገባ ሕገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፤” ሲሉም በጽሑፋቸው አመልክተዋል።
ኢዜማ በበኩሉ፣ ከምርታማነት እና የሀገራዊ ጸጥታ ጉዳዮችን ከመሳሰሉ ጉድለቶች በተጨማሪ፣ ይህን ፖሊሲ በማስፈጸም ሒደት ሊመጡ የሚችሉ ከፍተኛ ሕጸጾችን ለማስተናገድ “ዓቅም ያላቸው ተቋማት የሉም” አለመኖራቸውን ገልጾ፣ የፖሊሲ ማሻሻያው፥ “ጊዜያዊ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመፍታት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ነው፤” ሲል ተችቷል፡፡
ፓርቲው፣ “ፖሊሲ የማውጣት ሉዓላዊነትን የሚገድብ ማሻሻያ፣ ውጤቱ ቀውስ ጋባዥ ትርፉም አገራዊ ዕዳ ነው፤” ሲልም በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በሚመለከት፣ ትላንት ረቡዕ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ፣ ርምጃው በዘላቂነት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው፤ ብለዋል፡፡
ኾኖም፣ በአጭር ጊዜ የሚኖሩ የዋጋ ንረት ተጽእኖዎችን ለመቀነስ፣ መንግሥት የደመወዝ ጭማሬን እንዲሁም የተለያዩ የድጎማ ርምጃዎችን እንደሚወስድና ለዚኽም ተጨማሪ በጀት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
ይኹን እንጂ፣ ይህ የመንግሥት ርምጃ፣ “ለጊዜው ማስታገሻ ከመኾን ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል የመፍትሔ ሐሳብ አይደለም፤” ያለው ኢዜማ፣ ማሻሻያው ከመደረጉ አስቀድሞ ቅድመ ኹኔታዎች ሳይሟሉ ይህን መሰል ርምጃ በጥድፊያ ሊወሰዱ እንደማይገባ ብወተውትም “ሰሚ ጆሮ አላገኘኹም” ብሏል።
ስለኾነም፣ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ ለሚመጣው “ማንኛውም በሀገር እና በሕዝብ ላይ ለሚደርስ ምስቅልቅል፣ ውሳኔውን ያሳለፈው መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤” ሲል በመግለጫው አሳስቧል፡፡
“የለውጥ ሥራዎቻችን ስኬት ሁሉ በባለድርሻ አካላት የተባበረ ጥረት ላይ ይመሠረታል፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ይህም ምርታማነትን፣ የውጭ ንግድንና ገቢን ተባብሮ ማሳደግ ነው፤” ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ፣ ባንኮች የብርን የመግዛት ዓቅም ማዳከማቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ በንግድ ባንክ ከ80 ብር በላይ ተተምኖ የዋለ ሲኾን፣ ከግል ባንኮች ደግሞ የአንድ ዶላር ዋጋን ከ83 ብር በላይ የተመኑ አሉ፡፡
በተመሳሳይ፣ በዐዲስ አበባ ገበያ በተለያዩ የምግብ ዘይት ምርቶች እንዲሁም ከውጭ በሚገቡ የታሸጉ ምግቦች እና መጠጦች ላይ የዋጋ ጭማሬ መታየቱ እየተዘገበ ይገኛል፡፡ የከተማው ንግድ ቢሮ በበኩሉ፣ ዱቄትንና ዘይትን ጨምሮ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ፣ ያለበቂ ምክንያት ወቅቱን ያላገናዘበ የዋጋ ጭማሬ አድርገዋል ባላቸው 11 የመርካቶ ገበያ ነጋዴዎች ላይ፣ መደብራቸውን የማሸግ ርምጃ እየወሰደ መኾኑን አስታውቋል፡፡