የሐማስ የፖለቲካ ዘርፍ መሪ ኢስማኤል ሀኒዬ ኢራን ውስጥ ተገደሉ

ፍልስጤማውያን የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬ ኢራን ውስጥ ከተገደሉ በኋላ በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ ኬብሮን የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፣ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.

የሐማስ መሪው ኢስማኤል ሀኒዬ፣ እስራኤል፥ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት እንደተገደሉ፣ ዛሬ ረቡዕ አስታውቋል፡፡

ከንጋት በፊት የተገደሉት ሃኒዬ፣ ወደ ቴህራን የተጓዙት በዐዲሱ የኢራን ፕሬዚዳንት በዓለ ሢመት ላይ ለመገኘት እንደነበር ቡድኑ አስታውቋል፡፡

ሐማስ በቴሌግራም ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የፖለቲካ መሪው ሃኒዬ ቴህራን በሚገኝ የመኖሪያ ቤት መገደላቸውን አመልክቷል፡፡

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሚኔ፣ የሐማሱ መሪ ሌሊት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት እንደተገደሉ ተናግረዋል፡፡ ኾኖም ስለ ግድያው፣ ወዲያውኑ በዝርዝር የታወቀ ነገር የለም፡፡ “የሃኒዬን ግድያ እንበቀላለን” ያሉት አያቶላህ ኻሚኔ፣ እስራኤል “ለሚደርስባት ብርቱ ቅጣት ትዘጋጅ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

እስራኤል ግድያውን በሚመለከት ወዲያውኑ የሰጠችው አስተያየት የለም፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

የሐማስ የፖለቲካ ዘርፍ መሪ ኢስማኤል ሀኒዬ ኢራን ውስጥ ተገደሉ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ሲንጋፖር ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፣ ስለግድያው “የምናውቀውም ነገር የለም፡፡ እጃችንም የለበትም፤” ብለዋል፡፡ ግድያው በእስራኤል ጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ስለሚኖረው አንድምታ፣ ከወዲሁ ግምታዊ አስተያየት ለመስጠት እንደማይፈልጉም ተናግረዋል፡፡

ኾኖም ክሥተቱ፣ የፍልስጥኤማውያን ሲቪሎች ሥቃይ እንዲያበቃና የተቀሩት ብዛት ያላቸው ታጋቾች እንዲለቀቁ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በይበልጥ አስፈላጊ እንደሚያደርገው ብሊንከን አመልክተዋል፡፡

ቀጣዩ ዘገባ፣ በአሜሪካ ድምፅ እና በሌሎች የዜና አውታሮች የተጠናቀሩ ዜናዎችን አካቷል፡፡