በዐማራ ክልል ላይ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከተገባደደ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ልዩ ልዩ ክልከላዎች በክልሉ ርእሰ መዲና ባሕር ዳር ላይ ተጥለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታው ምክር ቤት፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ ባወጣው መግለጫ፣ በከተማው “ችላ የማይባሉ” ሲል የገለጻቸውን የጸጥታ ስጋቶች ለማስወገድ፣ በሰው እና በተሽከርካሪ ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡
የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲን በመወከል ከክልሉ ተመርጠው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት አቶ አበባው ደሳለው፣ “ተደጋጋሚ ክልከላዎችን ማድረግ ያለውን የጸጥታ ችግር አይፈታውም፤” ብለዋል፡፡
በዐማራ ክልል ለ10 ወራት ያህል ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የሥራ ጊዜ፣ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ከተጠናቀቀ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ የክልሉ መዲና ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ፣ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ልዩ ልዩ ክልከላዎችን መጣሉን አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታው ምክር ቤት፣ በጉዳዩ ላይ በመወያየት አሳለፍኹት ባለው ውሳኔው፣ በሰዎች እና በተሽከርካሪዎች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ገልጿል፡፡
በከተማው “ችላ የማይባሉ የጸጥታ ችግሮች አሉ፤” ያለው ምክር ቤቱ፣ ችግሩን ለመከላከል ያስችል ዘንድ ዝርዝር ክልከላዎችን ማስቀመጡን አመልክቷል፡፡
ምክር ቤቱ በክልከላው ከጣላቸው ገደቦች ውስጥ ሰውን ጨምሮ፣ የመንግሥት፣ የቤት እና ማንኛውም የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ከምሽቱ 3፡00 በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ከልክሏል።
Your browser doesn’t support HTML5
የባለሦስት እግር ባጃጆችን፣ ከምሽቱ 12 እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ማሽከርከር የተከለከለ ሲኾን፣ ባለሁለት እግር ሞተር ተሽከርካሪ ላልተወሰነ ጊዜ ማሽከርከር እንደማይቻል ዕቀባ ተጥሏል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከጸጥታ መዋቅሩ አባላት እና ለጸጥታ ሥራ ተሰማርተው የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሰዎች ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ማንኛውም የጸጥታ አባል፣ ከተሰጠው ስምሪት ውጭ በሚኾንበት ጊዜ ሲቪል ለብሶ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልና ሌሎች ክልከላዎችን መጣሉን ተጠቅሷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የጣለውን ክልከላ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን አንድ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ፣ “በከተማው እየታየ ካለው ወንጀል አንጻር ክልከላው ተገቢ ነው፤” ብለዋል፡፡
በዐማራ ክልል፣ በመንግሥት እና በፋኖ ቡድን ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ ላለፉት ዐሥር ወራት ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ያበቃ ቢኾንም፣ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መቀጠላቸውን በተለያዩ ጊዜያት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲን በመወከል ከክልሉ ተመርጠው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት አቶ አበባው ደሳለው፣ “ተደጋጋሚ ክልከላዎችን ማድረግ ያለውን የጸጥታ ችግር አይፈታውም፤” ብለዋል:
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት አናጋው ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ምላሻቸውን እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ፣ በቅርቡ ባወጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ በዐማራ ክልል ተጥሎ የነበረውንና በቅርቡ ያበቃውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አለማራዘማቸው ጥሩ ርምጃ መኾኑን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡