“ደቡባዊ ጋዛ ራፋህ የሚገኘው ዋናው የውሃ ማጠራቀሚያ መፍረሱ የጋዛ ሕዝብ ንጽሕናው ያልተጠበቀ ውሃ እንዲጠጣ ስለሚያስገድደው ለከፋ የተላላፊ በሽታዎች አደጋ ይዳረጋል” ሲሉ የተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሕጻናት መርጃ ዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጄምስ ኤልደር ጄኔቫ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል "እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሺዎች የተቆጠሩ ራፋህ ውስጥ የተጠለሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ውሃ ያገኙ የነበሩት ከዚያ ማጠራቀሚያ ጣቢያ እንደነበር ገልጸው፤ መፍረሱን ተከትሎ ህጻናት እና ቤተሰቦች ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃ እንዲጠጡ ይገደዳሉ። ለውሃ ጥም እና ለበሽታዎችም ይዳረጋሉ ብለዋል።
የእስራኤል ሃሬትዝ ጋዜጣ በትላንት ሰኞ ዘገባው ‘የእስራኤል ወታደሮች ከበላይ የደቡባዊ ዕዝ ሳይሆን በብርጌድ አዛዦቻቸው ትዕዛዝ ዋናውን የውሃ ማከፋፈያ ጣቢያ በፈንጂ አፍርሰውታል’ ብሏል።
ድራጊቱ ከዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት ጋር በተያያዘ በእስራኤል ወታደራዊ ፖሊስ ምርመራ የተከፈተበት መሆኑንም የሃሬትዝ ዘገባ አመልክቷል።