የኡጋንዳ ፖሊስ በብረት ሳጥን የተቀበሩ የራስ ቅሎችን ማግኘቱን አስታወቀ

  • ቪኦኤ ዜና

ከዋና ከተማይቱ ካምፓላ 39 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው ምፒጊ ከተማ

የኡጋንዳ ፖሊስ ለፈረንሣይ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጠው በብረት ሳጥን ተደርገው የተቀበሩ 17 የራስ ቅሎችን መሃል ሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኝ ቤተ መቅደስ አቅራቢያ ካለ ሥፍራ በቁፋሮ አውጥቷል።
ከዋና ከተማይቱ ካምፓላ 39 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከምትገኘው የምፒጊ ከተማ ወጣ ብሎ ካለው የካባንጋ መንደር አቅራቢያ የማገዶ እንጨት በመልቀም ላይ የነበሩ ሕጻናት የተባሉትን ሳጥኖች ትላንት ማግኘታቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጨማሪ የተቀበሩ የራስ ቅሎች ያለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ቁፋሮው መቀጠሉን አንድ የክልሉ ፖሊስ አባል ተናግረዋል። የሟቾቹን እድሜ እና ጾታ እንዲሁም የተቀበሩበትን ጊዜ ለማወቅ የራስ ቅሎቹ ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑም ተገልጧል።
በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የመደናገጥ ስሜት መፍጠሩን የገለጹት ባለስልጣናት ሕዝቡ እንዲረጋጋ እየጠየቁ ነው።
በሌላ በኩል ባብሳ በተባሉ ታዋቂ የንግድ ሰው ላይ ካምፓላ ውስጥ ባለፈው የጥር ወር የተፈጸመው ግድያ ግለሰቡ ከሥራ ወደ መኖሪያቸው በሚመለሱበት ወቅት በተቀጠሩ ታጣቂዎች መፈጸሙ ተዘግቧል።