ብሩህ አፍሪካውያን ወጣቶችንና የመጪ ዘመን መሪዎችን የሚያስተሳስረው የማንዴላ ዋሺንግተን ፌሎሺፕ ዓመታዊ ጉባኤ፣ ዛሬ ሰኞ በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ ተጀምሯል።
በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር የሚሰናዳው ጉባኤው፣ ዘንድሮ 10ኛ ዓመቱን የያዘ ሲኾን፣ በእስከ አሁኑ ቆይታው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች ከኾኑ ሀገራት የተውጣጡ 700 ያህል ወጣት መሪዎችን አሳትፏል።
የወጣት አፍሪካውያን መሪዎች ትስስር መርሐ ግበሩ በምኅጻሩ ያሊ ውስጥ ተሳታፊ የሚኾኑት ወጣቶች፣ በየሀገራቱ በሚደረጉ ልዩ ውድድሮች የሚመረጡ ናቸው፡፡ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመጡ በኋላ ለስድስት ሳምንታት ከ20 በላይ በኾኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የቀለም ትምህርት እና የአመራር ሥልጠናዎችን ይወስዳሉ።
በተጨማሪ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋራ ትስስር የሚፈጥሩባቸው መርሐ ግብሮች ይዘጋጅላቸዋል።
የትስስር መርሐ ግብሩ ግብ፥ "የአፍሪካ አህጉርንና የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝቦችን የሚጠቅሙ ዐዲስ እድሎችን የሚያበረክቱ ግንኙነቶችን መፍጠር” እንደኾነ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያሰራጨው የፕሬስ ማስገንዘቢያ ያሳያል።
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ በሚከናወኑ የሦስት ቀናት ጉባኤዎች ላይ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድን ጨምሮ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት እና የኪነ ጥበብ ሰዎች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የአሜሪካ ድምፅ የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ከኾኑ ወጣቶች ጋራ የሚያደርጋቸውን ቃለ መጠይቆች እና ውይይቶች በቀጣይ ቀናት ውስጥ ያቀርባል።