የቻይናው ሺ እና የጣልያኗ ሜሎኒ ቤጂንግ ውስጥ መከሩ

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በቤጂንግ ሲወያዩ፣ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዩክሬን ጦርነት እና በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ዛሬ ሰኞ ቤጂንግ ውስጥ መወያየታቸውን የሜሎኒ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ሀገራቸው የወቅቱን የቡድን 7 ፕሬዚዳንትነት ቦታ የያዘችው ሜሎኒ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ዓለማቀፋዊ የጸጥታ ችግርን ለመቋቋም ቻይና እንደ አጋር ያላትን ጠቀሜታ በንግግራቸው አሳስበዋል።

ሁለቱ መሪዎች "ከዩክሬን ጦርነት ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታዎችን የበለጠ ሊያባብስ እስከሚችለው ስጋት ያሉትን ጉዳዮች በማንሳት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ዙሪያ ተነጋግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች በኢንዶ-ፓሲፊክ ውስጥ እየጨመረ ስላለው ውጥረት መወያየታቸውን የጣሊያኑ መሪ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት በምዕራቡ ዓለም እና በዓለም ሁለተኛዋ ትልቁ ኢኮኖሚ በሆነችው መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እያሽቆለቆለ በመጣበት ወቅት፣ ጣሊያን የሺ ትልቁ መታወቂያ ፕሮጀክት ከሆነው ፣ የቤልት ኤንድ ሮድ ተነሳሽነት መሳተፏን አቋርጣለች፡፡ ሜሎኒ ከዚያ ወዲህ እያሽቆለቆለ የመጣውን የሀገራቸውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ከቤጂንግ ጋር ያላቸውን ትስስር ማሳደግ ፈልገዋል፡፡

“በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣ ትልቅ አለመረጋጋት አለ፡፡ ይህንን ውስብስብና ተለዋዋጭ ጉዳይ ለመቋቋም ቻይና እጅግ አስፈላጊ መሆኗ አይቀርም ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ሜሎኒ ቤጂንግ ውስጥ የቻይናውን መሪ ባነጋገሩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ጣልያን ከዚህ ቀደም ከቤጂንግ ጋር ባደረገችው የተናጥል ስምምነት የተነሳ፣ ለቻይና ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ልትሰጥ የምትችል ሲሆን በህብረቱም ውስጥ የተሻለ ድምጽ በማሰማት ቻይናን ልታግዝ እንደምትችል በሮይተርስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡

እኤአ በ2019 በኢንደስትሪ ከበለጸጉት የቡድን 7 ሀገራት መካከል የቻይናን ቤልት ኤንድ ሮድ መሠረት ልማት ተነሳሽነት በመቀላቀል ጣልያን ብቸኛዋ ሀገር ነበረች፡፡

ምንም እንኳ ጣልያን ከተነሳሽነቱ በዩናትይድ ስቴትስ ግፊት የወጣች ቢሆንም አሁንም ድረስ ከቻይና ጋር የንግግድ ትስስር ለመፍጠር ጠንካራ ፍላጎት ያላት መሆኑን ትላንት እሁድ በፈረመችው የሶስት ዓመት የድርጊት መርሃ ግብር አመላክታለች፡፡